ኢሳት (ታህሳስ 29 ፡ 2008)
ኢትዮጵያውያን በፍቅርና በሰላም ተከባብረው እንዲኖሩ፣ አድነታቸውን እንዲጠብቁ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ አቡነ መሮቆርዮስ ጥሪ አቀረቡ፥ በኦሮሚያ ክልል ለተቃውሞ አደባባይ በወጡ ኢትዮጵያውያን ላይ መንግስት በወሰደው የመግደልና የእስር እርምጃ ማዘናቸውን ገልጸው፣ ለሟች ለቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል።
ፓትሪያርኩ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ የኢየሱስ ክርስቶስን 2ሺ 8ኛ አመት የልደት በዓል በማስመልከት ለኢትዮጵያውያን ትናንት ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያ ግዛት ወደሱዳን ተላልፎ ሊሰጥ መሆኑን በማስመልከት እንዲሁም በኢትዮጵያ የተከሰተውን ርሃብ በተመለከተ መልዕክት አስተላልፈዋል።
መቀመጫቸውን በዋሽንግተን ዲሲ ያደረጉትና በስደት የሚገኘውን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሚመሩት ፓትሪያርክ አቡነ መርቆርዮስ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል መልዕክታቸው ኢትዮጵያውያን በመተሳሰብ፣ በመቻቻልና፣ በአንድነት እንዲፀኑ መልዕክት አስተላልፈዋል።
“የኢትዮጵያ ህዝብ በሰላምና በፍቅር የሚኖረው፣ ለራሱም ሆነ ለሌላው መድሃኒት የሚሆነው ተከባብሮ በአንድነት ሲኖር ነው” ያሉት ቅዱስ ፓትርያርኩ፣ በኦሮሚያ ክልል በተማሪዎችና በሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ በተፈጸመው ግድያም ማዘናቸውን ገልጸዋል።
“ሰላማዊ ሰልፍ በወጡ ኢትዮጵያውያን ላይ መንግስት በወሰደው ዕርምጃ ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን ላጡት ኢትዮጵያውያን ወገኖች ሁሉ የተሰማንን ጥልቅ ሃሰን እየገለፅን ለቤተሰቦቻቸው መፅናናንትን እንዲያድልልን እንጸልያለን” በማለት ለሟች ቤተስሰቦች የማፅናኛ መልዕክት ያስተላለፉት ፓትርያርክ አቡነ መርቆርዮስ፣ በመከራም ሆነ በደስታ ጊዜ ህዝቡ እርስ በእርሱ እየመከረ አገሩን በንቃትና በአንድነት እንዲጠብቅ የአደራ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የሃገራችንን ለም መሬት ለሱዳን አሳልፎ ለመስጠት ስልጣን ላይ ያለው መንግስት በሃገራችን ላይ የጥፋትና የበደል ስራ እንዳይሰራ ሲሉ ያሳሰቡት ፓትሪያርክ አቡነ መርቆርዮስ፣ “በራሳቸው ሃገርና መሬት ላይ አርሰው የሚበሉትን ድሃ ገበሬዎች ለማፈናቀል ከሱዳን ወታደር ጋር ተባብሮ አራሽ ገበሬዎች የሚያፈናቅል ሰራዊት መላኩ ታሪክ የሚያጎድፍ አሳዛኝ ክስተት ነው” በማለት የህልውና ጉዳይ በመሆኑ ሁሉም ተግቶ እንዲሰራበት ጥሪ አቅርበዋል።
“በርሃብ አለንጋ በመግረፍ ላይ ያለውን ህዝባችንን በዓል ልደቱን ምክንያት በማድረግ ክርስቲያኖች ሁሉ እንዲያሳስቧቸው’ ሲሉ ጥሪ ያቀረቡት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መሮርዮስ “የልደት በዓሉን ረሃብረተኞች በመመገብ፣ ስደተኞችን በማፅናናት እንዲያከብሩለት ቤተክርስቲያን ጥሪ ታስተላልፋለች” ብለዋል።