የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ በእኛ ስራ ምን አገባችሁ ሲሉ የመንግስት ባለስልጣናትን ተቃወሙ

(ኢሳት ዜና –ሐምሌ 17/2009)በሳምንቱ መጨረሻ አርብ ሐምሌ 14/2009 የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትሩ አቶ ካሳ ተክለብርሃንና ሌሎች ባለስልጣናት ከአባቶቹ ጋር ያደረጉትን ውይይት በተመለከተ ዝርዝር መረጃን ይዞ የወጣው በቤተክርስቲያኒቱ ጉዳይ ላይ የሚያተኩረው ሃራ ተዋህዶ የተባለው ድረ ገጽ ነው።

በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ አሉ የሚባሉ ችግሮችን መነሻ ባደረገው ውይይት ላይ የመንግስት ባለስልጣናት መገኘታቸውን አንዳንድ አባቶች ቢደግፉም፣ፓትሪያርኩን ጨምሮ ሌሎች አባቶች ግን ተቃውሞ ማሰማታቸውን ዘገባው አመልክቷል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹእ አቡነ ማቲያስ በእኛ ስራ ምን አገባችሁ በማለት የባለስልጣናቱን በጉባኤው ላይ መገኘት ተቃውመዋል።

ፓትሪያርኩ ይህ ጣልቃ ገብነት ነው ሲሉም አጥብቀው መቃወማቸውን ከዘገባው መረዳት ተችሏል።

እናንተ አዛዥ ሆናችሁ እኔን ተላላኪ ልታደርጉኝ አትችሉም በሚል ጠንካራ አስተያየታቸውን በጉባኤው ላይ ሰንዝረዋል።

በጉባኤው ላይ የተገኙት ሌሎች አባቶች በየተራ በቤተክርስቲያኒቱና በምእመናኑ ላይ እየደረሰ ነው ያሉትን በደል ለመንግስት ባለስልጣናቱ አሳስበዋል።

የወላይታ፣ኮንታና ዳውሮ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ አቡነ ማቲዎስ እናንተ ባመጣችሁብን ዘረኝነት ህዝቡ ሊፋጅ ነው ሲሉ  ያደረባቸውን ስጋት ገልጸዋል።

ህዝቡ ልቦና ውስጥ ዘረኝነትን ካስገባችሁ በኋላ ዘረኝነትን እናጥፋ ትላላችሁ በማለትም ወቅሰዋል።

የአባቶቹን ተቃውሞና ትችት ያስተናገዱት የመንግስት ባለስልጣናት እሺ ቅዱስ አባታችን ጸሎት ያድርጉልን ሲሉ መመለሳቸውን ከሀራ ተዋህዶ ዘገባ መረዳት ትችሏል።