የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አቶ ኢሳያስ ጅራን ፕሬዝዳንት አድርጎ መረጠ

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 27/2010)የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከኦሮሚያ ክልል የተወከሉትን አቶ ኢሳያስ ጅራን ፕሬዝዳንት አድርጎ መረጠ፡፡

የ46 ዓመቱ አቶ ኢሳያስ ጅራ ከጠቅላላው 145 ድምፅ 87 በማግኘት በአፋር ሰመራ በተካሄደው ምርጫ ሲያሸንፉ አቶ ተካ አስፋው ደግሞ ምርጫውን በሁለተኝነት አጠናቀዋል።

በውድድሩ የተካፈሉት ተሰናባቹ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻና አቶ ተስፋይ ካሕሳይ ከሁለተኛው ዙር ምርጫ ቀድመው ራሳቸውን ማግለላቸው ታውቋል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ለመምረጥ ቀድሞ በተደረገ የመጀመሪያ ዙር ምርጫ አቶ ኢሳያስ ጅራ ከፍተኛውን ድምፅ አግኝተው ነበር፣ በፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ግን ከ50 በመቶ ድምፅ በላይ ባለማግኘታቸው ምርጫው በድጋሚ ተካሄዷል፡፡

በዚህም መሠረት በሁለተኛው ዙር ምርጫ አቶ ኢሳያስ 87 ድምፅ ሲያገኙ፣ አቶ ተካ አስፋው ደግሞ 58 ድምፅ አግኝተዋል፡፡

እናም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከኦሮሚያ ክልል የተወከሉትን አቶ ኢሳያስ ጅራን ፕሬዚዳንት አድርጎ መርጧል ፡፡

የምክትል ፕሬዝደንትና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ምርጫም ተከናውኗል።

የፌዴሬሽኑ ምርጫ ወዝግብ የነበረበት በመሆኑ ለአራት ጊዜ ያህል በፊፋ ትዛዝ እንዲራዘም ሲደረግ ቆይቷል።

በመጀመሪያው ዙር ምርጫ አነስተኛ ድምፅ አምጥተው የነበሩት ተሰናባቹ ፕሬዝደንት አቶ ጁነዲ ባሻና አቶ ተስፋይ ካሕሳይ ከሁለተኛው ዙር ምርጫ ራሳቸውን አግልለዋል።

በመጨረሻም አቶ ኢሳያስ 87 ድምፅ ወይንም 66 በመቶውን በማምጣታቸው የፌዴሬሽኑን ፕሬዝዳንት ሆነዋል።

ይሕ በእንዲህ እንዳለም የሥራ አስፈፃሚና የምክትል ፕሬዝዳንት ምርጫ ተካሂዶ  ኮለኔል አወል አብዱራሂም የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ተመርጠዋል።

የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላትም ታውቀዋል፤ የቀድሞው የብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ ሰውነት ቢሻውም በኮሚቴው ውስጥ እንደተካተቱ ለማወቅ ተችሏል።

አቶ ኢሳይያስ የጅማ ከተማ ክለብ ፕሬዝዳንት፣ የሰበታ ከተማ ክለብ ስራ አስኪያጅ እንዲሁም የጅማ ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።

የፌዴሬሽኑ ኃላፊ ሆነው ከመመረጣቸው በፊት የጅማ አባጅፋር ስራ አስኪያጅ ሆነው በመስራት ላይ ነበሩ።