የኢትዮጵያ እና ኤርትራ መሪዎች በሁለቱ አገራት ድንበሮች ላይ ተገኝተው አዲሱን አመት በማክበር ድንበሮችን ከፈቱ
( ኢሳት ዜና መስከረም 01 ቀን 2011 ዓ/ም ) ለላፉት 20 ዓመታት የአዲስ ዓመት በአልን በምሽግ ሲያሳልፉ የነበሩት የሁለቱ አገራት ወታደሮች ጠ/ሚኒስትር አብይ አህመድና ፕ/ት ኢሳያስ አፈወርቂ በተገኙበት በቡሬ እና በዛላንበሳ ግንባር በአሉን አክብረዋል።
ቡሬ ግንባር ያለውን ድንበር ከከፈቱ በሁዋላ መሪዎቹ ወደ ዛላንበሳ ግንባር በማምራት በዓሉን በስፍራው ከሚገኙ የሰራዊት አባላት እንዲሁም በሁለቱ አገራት ከሚገኙ የኢሮብ ተወላጆች ጋር ድንበር በመክፈት አክብረዋል።
“ ዛሬ ምሽጉን አፍርሰን በጋራ ዳስ ጥለናል” ያሉት ዶ/ር አብይ፣ የየብስ አገልገሎት መጀመሩንም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ከዛሬ ጀምሮ ወደ ካምፕ ተመልሶ የሚያገግምበት እና ራሱን የሚያደራጅበትና የሚያበቃበት ስራ እንደሚሰራ” ዶ/ር አብይ ገልጸዋል።
ጠ/ሚኒስትር አብይ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት የተጀመረው የሁለቱ አገራት ግንኙነት እያደገ በመሄድ ላይ ሲሆን፣ ያለ ውጭ አገር ሸምጋይ ሁለቱ አገራት ልዩነታቸውን በሰላም ለመፍታት የሚሄዱበትን መንገድ የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ በርካታ አገሮች አድናቆታቸውን እየገለጹ ነው።
ዶ/ር አብይ የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናትንና የተቃዋሚ መሪዎችን እንዲሁም ኤርትራውያንን በሚሊኒየም አዳራሽ በመጋበዝ የአዲስ አመት ዋዜማን አብረው አሳልፈዋል። ጠ/ሚኒስትሩ 2010 “ ኢኮኖሚው ወደቀውስ የገባበት- ማሕበራዊ ሕይወታችን ለሽብር የተጋለጠበት- ወጣቶች በአመፅ ሠልፍና በሞት ጥላ ስር የዋሉበት- ወህኒ የተዘጋባቸው የሠቆቃ ድምፆች ገንነው የተሰሙበት አስጨናቂና ከባድ ዓመት ነበር።” ብለዋል። “ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ዜጎች ከቀያቸው የተፈናቀሉበት፣ ሰብዓዊ ቀውስ ጣራ የነካበት፣ አንድነታችን በልዩነት መጋዝ ተገዝግዞ የሰለለበት “ ከባድ አመት ማለፉን የተናገሩት ዶ/ር አብይ፣ “እጅግ ደስ የሚለው ግን አሁን እየሄድን ያለነው ወደ ተስፋ፣ ወደ ብርሃን፣ ወደ ይቅርታና ወደ ፍቅር መሆኑ ነው” ሲሉ፣ አዲሱ አመት መልካም ተስፋ ይዞ መምጣቱን ገልጸዋል።
“ አዲስ ዘመንን እያከበርን በትናንቱ የምንጨቃጨቅ ከሆነ ዘመኑ እንጂ እኛ አልተቀየርንም ማለት ነው! ከትናንትናው ሳንወጣ እንዴት ነው ዛሬን የምናከብረው? ፊትን ወደ ትናንት አዙሮ እንዴት ነው ወደ ነገ መጓዝ የሚቻለው?” የሚለውን ጥያቄ ያነሱት ጠ/ሚኒስትሩ፣ “ ከየትኛውም ሕዝብ ባልተናነሰ መልኩ ክፋትን አስተናግደናል፡፡ በጥላቻ ተመላልሰናል፤ ቆስለንም ሞተንም ትናንትን አሳልፈናል። ከእንግዲህ ግን በውስጣችን የተረፈ አቅም ካለ መጥላትም ሆነ መጠላት የሚኖርበት ፊታችን የተደቀነው ድህነት፣ በሽታ፣ እርዛትና ድንቁርና ብቻ እንጂ ሌላ ኢትዮጵያዊ ሊጠላም፣ ሊገፋም አይገባም” ብለዋል። “በውስጣችን የተረፈው አቅም ከእንግዲህ መዋል ያለበት መጠላለፍና አሻጥርን ለመጥላት፣ ፍትህና እኩልነትን ለማፅናት፣ የሕግ የበላይነትና የዴሞክራሲ ባህልን ለመገንባት፣ ምርጫን እውነተኛና ዴሞክራሲያዊ ለማድረግ መሆን ይኖርበታል።” ሲሉ የወደፊቱን ራዕያቸውን ገልጸዋል።