(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 22/2011)የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት መጅሊስ ስራ አመራር ሃላፊነቱን ሊያስረክብ መሆኑን አስታወቀ።
የመጅሊስ አመራር ስልጣኑን እንደሚለቅ ያስታወቀው እየተካሄደ ባለው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ነው።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች አይወክለንም በሚል ለአራት አመታት ሲቃወሙት የነበረው የመጅሊስ አመራር ስልጣኑን በነገው እለት እንደሚያስረክብ ፕሬዝዳንቱ ማስታወቃቸውን ሬዲዮ ፋና ዘግቧል።
በትላንትናው ዕለት በገዛ ፈቃዳቸው ስልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ ያቀረቡት የመጀሊሱ ፕሬዝዳንት ሼህ መሀመድ አሚን ጀማል ጥያቄአቸው ውድቅ እንዲሆን መደረጉ የሚታወስ ነው።