የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት በግማሽ ሊቀንስ ይችላል ተባለ

ኢሳት (ህዳር 13 ፥ 2009)

የአለም ባንክ በተያዘው የፈረንጆች አመት የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት በመንግስት ከተቀመጠው በግማሽ ሊቀንስ እንደሚችል ይፋ አደረገ።

ባለፈው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስቶ አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ የሃገሪቱ ዕድገት በ12 በመቶ ያድጋል ሲሉ ለሃገር ውስጥ በመገናኛ ብዙሃን ብዙሃን መግለጻቸው ይታወሳል።

ይሁንና የኢትዮጵያ ዋነኛ የልማት አጋር የሆነው የአለም ባንክ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሩዋንዳና ታንዛኒያ በአማካኝ የስድስት በመቶ የኢኮኖሚ እድገት ሊያስመዘግቡ ይችላሉ ሲል በኢትዮጵያ መንግስት የተሰጠውን ትንበያ በግማሽ ያህል ቀንሶታል።

በአለም ገበያ የተመዘገበ የገበያ መዋዠቅ ጠንካራ የፋይናንስ ቁጥጥር እና ተያያዥ ጉዳዮች የሰብ ሰሃራ አፍሪካ ኢኮኖሚ ዕድገት የተጠበቀውን ያህል ዕድገት እንዳያስመዘግቡ ተፅዕኖ ማሳደሩ ባንኩ ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል።

በአጠቃላይ በሰብ ሰሃራ አፍሪካ የሚገኙ ከ15 በላይ ሃገራት የኢኮኖሚ እድገታቸው በ1.6 በመቶ ይቀንሳል ተብሎ የተጠበቀ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ሩዋንዳና ታንዛኒያ ከቀጠናው የተሻለ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ይመዘገብባቸዋል ተብሎ ተገምቷል።

ባለፈው ሳምንት በወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫን የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የተለያዩ መሰናክሎች ቢያጋጥሙትም 12 በመቶ እድገት ይመዘገባል ሲሉ ተናግረዋል።

የአለም ባንክና የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች በበኩላቸው በኦሮሚያ ክልል ለአንድ አመት ያህል ጊዜ የዘለቀውና በቅርቡ በአማራ ክልል የተቀሰቀሰው ሃዝባዊ ተቃውሞ በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ይገልጻሉ።

በህዝባዊ ተቃውሞ ምክንያት የኢትዮጵያ የግብርና ምርት እድገት በሶስት በመቶ አካባቢ ቅናሽ ማሳየቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢያሳውቁም፣ የሃገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት የሚደርስበት ችግር አይኖርም ሲሉ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

ካለፉት ሶስት አመታት ወዲህ የኢትዮጵያ ውጭ-ንግድ እየቀነሰ መምጣትና የሃገሪቱ የአለም አቀፍ ብድር ከተጠበቀው በላይ መሆን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚን ክፉኛ እየተፈታተነ እንደሚገኝ የአለም ባንክ መረጃ የመለክታል።

እስካለፈው ነሃሴ ወር የኢትዮጵያ አጠቃላይ የብድር እዳ ወደ 36 ቢሊዮን ዶላር አካባቢ የተመዘገበ ሲሆን፣ የብድሩ መጠን እየጨመረ መሄድ በውጭ ምንዛሪ ክምችትና በኢኮኖሚ ዕድገቱ ላይ ጫና ማሳደሩን የፋይናንስ ተቋማት ይገልጻሉ።

በቀጣዩ የፈረንጆች አመት የአለም የንግድ እንቅስቃሴ የሚፈለገውን ያህል መነቃቃት ያሳያል ተብሎ ባለመጠበቁ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአፍሪካ ሃገራት ኢኮኖሚ ዕድገት የተሻለ ለውጥ እንደማይጠበቅበት የፋይናንስ ተቋማቱ አክለው አስታወቀዋል።