ኢሳት (ጥር 18 ፥ 2009)
ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ የመንገደኞች አውሮፕላን ከአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ወደ አዲስ አበባ ከተማ በመብረር ላይ እንዳለ በተሳፋሪ ላይ አጋጥሟል በተባለ የጤና ችግር አቅጣጫን ቀይሮ በካናዳ ለማረፍ ተገደደ።
ይኸው የመንገደኞች አውሮፕላን አቅጣጫውን ከቀየረ በኋላ በካናዳው ሴንት ጆን አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ማረፉን የድርጅቱ ቃል አቀባይ ኤሪካ ኬላንድ ለካናዳ የማሰራጫ ጣቢያ (CBC) ገልጸዋል።
ይሁንና ቃል አቀባዩዋ አጋጥሟል የተባለው የጤና እክል በአውሮፕላኑ የበረራ አባላት ያጋጠመ ይሁን በመንገደኞች ላይ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ላይ የነበረው ይኸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላን ረቡዕ ዕኩለ ቀን አካባቢ ከዋሽንግተን ዲሲ የዳለስ አየር ማረፊያ ጣቢያ ከተነሳ በኋላ በሰዓታት ልዩነት በካናዳ እንዲያርፍ መገደዱን መገኛኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
የሴንት ጆን አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ቃል አቀባይ የመንገደኞች አውሮፕላን ለምን ያህል ጊዜ በስፍራው እንደሚቆይ አለመታወቁን ለጋዜጠኞች አስታቀዋል።
ይኸው አውሮፕላን ምን ያህል ጊዜ መንገደኞችን አሳፍሮ ይጓዝ እንደነበረም የተገለጸ ነገር የሌለ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድም በጉዳዩ ዙሪያ እስካሁን ድረስ የሰጠው ምላሽ የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በዚሁ መንገደኛ አውሮፕላን ተሳፋሪ የነበሩ እማኞች አውሮፕላኑ ተገዶ በካናዳ ለማረፍ የተገደደው አንድ ኢትዮጵያዊ መንገደኛ ህመም አጋጥሟቸው እንደነበር ለኢሳት አስታውቋል።
መንገደኛዋ በካናዳ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ቢደረግም፣ ስማቸው ያልተገለጹት ኢትዮጵያዊት ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል።
የመንገደኞቹ አውሮፕላን ከሰዓታት መዘግየት በኋላ የሟች አስከሬንን በመያዝ አዲስ አበባ ዘግይቶ መድረሱንም ከምንጮች ለመረዳት ተችሏል።