ኢሳት (ጥቅምት 30 ፥ 2009)
ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ የመንገደኞች አውሮፕላን ከ300 በላይ መንገደኞችን አሳፍሮ ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ በማቅናት ላይ እንዳለ በፓኪስታን በቴክኒክ ችግር ተገዶ አረፈ።
335 መንገደኞችንና 12 የበረራ ባለሙያዎችን አሳፍሮ የነበረው አውሮፕላን በነዳጅ መያዣው ላይ የነዳጅ መፍሰስ አጋጥሞት በአስቸኳይ ለማረፍ መገደዱን የፓኪስታን የአቪየሽን ባለስልጣናት ረቡዕ ይፋ አድርገዋል።
የመንገደኞች አውሮፕላኑ በፓኪስታን የፑንጃብ ግዛት በምትገኘው የላሆር ከተማ አለም አቀፍ የመንገደኞች ማረፊያ ጣቢያ ከሙሉ ተሳፋሪዎች በሰላም ማረፉን ዳውን የተሰኘ የፓኪስታን ጋዜጣ ዘግቧል።
ከቻይና መዲና ቤጂንግ ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ላይ የነበረው የመንገደኞች አውሮፕላን አብዛኞቹ ቻይናዊያንና አፍሪካዊያን መንገደኞችን አሳፍሮ እንደነበር ታውቋል።
በአውሮፕላን ላይ ያጋጠመውን ይህንኑ የነዳጅ መፍሰስ ችግር ተከትሎም ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ላይ የነበሩ መንገደኞቹ በላሆር ከተማ በጊዜያዊነት እንዲያርፉ ተደርጎ አማራጭ ጉዞ እየተመቻቸላቸው መሆኑን የፓኪስታን ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርገዋል።
ባለፈው አመት ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ የመንገደኞች አውሮፕላን በአየርላንድ ደብሊን በቴክኒክ ችግር ለማረፍ ተገዶ እንደነበርም የሚታወስ ነው።
በፓኪስታ ለማረፍ ስለተገደደው የመንገደኞች አውሮፕላን በተመለከተ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እስካሁን ድርስ የሰጠው ምላሽ የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለም ንብረትነቱ የህንድ አየር መንገድ የሆነ የመንገደኞች አውሮፕላን በተመሳሳይ ሰአት ማክሰኞ በፓኪስታን ካራቺ ግዛት በአንድ መንገደኛ መታመም ምክንያት ተገዶ ለማረፍ መገደዱ ታውቋል።
ከህንድ ወደ ኳታር በማቅናት ላይ በነበረው የመንገደኞች አውሮፕላን ውስጥ ድንገተኛ የልብ ህመም አጋጥሞት ነበር የተባለው ተጓዥ ህይወቱ በአውሮፕላኑ ውስጥ ማለፉን የፓኪስታን አቪየሽን ባለስልጣናት ለመገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።
የመንገደኛውን አስከሬን ከአውሮፕላኑ ውስጥ እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ አውሮፕላኑ ጉዞውን ወደ ጓታር መቀጠሉም ታውቋል።