የኢትዮጵያ አየር መንገድ ናይጀሪያውያን ፓይለቶችን አሰልጥኖ ለመቅጠር እቅድ መያዙን አስታወቀ

ኢሳት (ጥቅምት 26 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለተለያዩ የበረራ መስመሮች ናይጀሪያውያን ፓይለቶችን ለማሰልጠንና ለመቅጠር እቅድ መያዙን አስታወቀ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጀምሮ የውጭ ሃገር ዜጎችን በተለያዩ የበረራ ዘርፎች እያሰማራ የሚገኘው አየር መንገዱ ለሃገር ውስጥ ተማሪዎችና ባለሙያዎች ቅድሚያን አልሰጠም በሚል ትችት ሲቀርብበት መቆየቱ ይታወሳል።

70ኛ አመት የምስረታ በዓሉን ለማክበር በናይጀሪያ ሌጎስ ከተማ ዝግጅት የአየር መንገዱ ተወካዮች ናይጀሪያዊያን ፓይለቶችን ለማሰልጠንና ለመቅጠር አዲስ እቅድ መያዙን ይፋ እንዳደረጉ ፓንች የተሰኘ የናይጀሪያ ጋዜጣ ረቡዕ ዘግቧል።

በናይጀሪያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ተወካይ የሆኑት አቶ ሰለሞን በጋሻው ሰልጥነው የሚቀጠሩት ናይጀሪያዊያን በተለያዩ የበረራ መስመሮች ላይ እንደሚሰሩ ገልጿል።

ይሁንና ተወካዩ በአዲሱ እቅድ ምን ያህል ፓይለቶችን ለማሰልጠንና ለመቅጠር ዝግጅት እንደተደረገ የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ድርጅቱ የውጭ ዜጎችን በሚቀጥር ጊዜ የተሻለ ክፍያን እና የማረፊያ ቤት ጥቅማጥቅምን እንደሚያቀርብ በመግለጽ ድርጊቱ አግባብ እንዳልሆነ ሲገልፁ ቆይተዋል።

አየር መንገዱ ፓይለቶችን ጨምሮ የበረራ አስተናጋጆችን ከቻይና እና ከሌሎች ሃገራት መቅጠሩንም ሰራተኞች ይገልጻሉ።

ባለፈው አመት ኪሳራ የደረሰበት የኬንያ አየር መንገድ ስራ የፈቱ የበረራ ባለሙያዎችን በውሰት ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመስጠት ፍላጎት እንዳለው ማስታወቁ ይታወሳል።

የኬንያው አየር መንገድ ከደረሰበት ኪሳራ በሚያገገም ጊዜ በውሰት የሰጣቸውን ፓይለቶች መልሶ እንደሚወስድ ከወራት በፊት አስታውቋል።

ይሁንና የኢትዮጵያም ሆነ የኬንያ አየር መንገድ የፓይለቶቹ ውሰት መቼ እንደሚካሄድ እና ምን ያህል ባለሙያዎች ተሳታፊ እንደሚሆኑ የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።