የኢትዮጵያ አየር መንገድ በዘረኝነት እየተወነጀለ ነው

መስከረም ፲፯ (አስራ ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአጼ ሃይለስላሴ ዘመን ስራውን የጀመረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ በትርፋማነቱ በተለያዩ አለማቀፍ የንግድ ተቋማት እየተመሰገነ ቢመጣም፣ የድርጅቱ ሰራተኞች ” ከዘረኝነት ጋር በተያያዘ ክሶችን እያቀረቡ ነው። አየር መንገዱ ጀምሮት ከነበረው የቁልቁለት ጉዞ የታደጉት አቶ ግርማ ዋቄ ስራቸውን ከለቀቁ በሁዋላ፣ በምትካቸው የተሾሙት አቶ ተወልደ ገብረማርያም ፣ ድርጅቱን ሙሉ በሙሉ በአንድ ብሄር ሰዎች ለማስያዝ እንቅስቃሴ መጀመራቸው፣ በትግራይ ብሄር ተወላጆችና በሌሎች ብሄር ተወላጆች መካከል ከፍተኛ የሆነ አድልዎ እየታዬ መምጣቱን እንዲሁም የህወሃት/ኢህአዴግን የፖለቲካ ፍልስፍና የማይከተሉ ኢትዮጵያውያን እድገት ይከለከላሉ፣ ከስራ ይባረራሉ ፣ ተቃዋሚ ናቸው ተብለው ከተጠረጠሩም ይታሰራሉ።
አንዳንድ ሰራተኞች ” አየር መንገዱን ከዘረኝነት” እንታደገው በማለት በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርቡም የሚሰማቸው አላገኙም። በዚህም የተነሳ ብዙዎቹ ሁኔታዎችን አመቻችተው ድርጅቱን እየለቀቁ ወደ አረብ አገራት፣ አውሮፓና አሜሪካ ይሰደዳሉ። አየር መንገዱ በአንጻራዊ መልክ ከሌሎች የአፍሪካ አየር መንገዶች ተሽሎ መገኘቱ ፣ የውስጥ ችግሩ ጎልቶ እንዳይነገር እንዳደረገው የሚገልጹት ሰራተኞች፣ በተለይ ስራ አስኪያጁ ድርጅቱን እንደ ኢፈርት ሁሉ የህወሃት ንብረት እያደረጉት ነው ይላሉ።
ሰራተኞች እንደሚገልጹት በቅርቡ የኢንፎሜሽን ክፍሉን እንደገና እናደራጃለን በሚል ቦታ ከተቀጠሩት መካከል 80 በመቶው የትግራይ ተወላጅ የህወሃት አባላት ናቸው። የአየር መንገዱ ዋና የኢንፎርሜሽን ኦፊሰር በቅርቡ በጡረታ ሲገለል፣ እሱን ተከትሎ የተቀጠረው ምህረተ አብ ተክላይ ነው። ምህረተአብ በአየር መንገዱ ስራ ከጀመረ 4 አመታት ብቻ የቆየ ቢሆነውም፣ በሶፍት ዌር ኢንጂነሪንግ ከ15 እስከ 25 አመታት ልምድ ላላቸው የድርጅቱ ሰራተኞች ሃላፊ ሆኖ መሾሙ ዘረኝነቱ እየከፋ መምጣቱን ማሳያ ነው በማለት ይናገራሉ። ከ4 አመታት በፊት አቶ ተወልደ የአየር መንገዱ ስራ አስኪያጅ ሲሆኑ በወጣው ክፍት የስራ ቦታ 10 የኮምፒተር ሳይንስ ተማሪዎች ሲቀጠሩ፣ ከ10ሩ ውስጥ 8 ቱ ከመቀሌ ዩኒቨርስቲ የተመረቁ የትግራይ ብሄር ተወላጆች መሆናቸውን፣ ከእነሱ መካከል ደግሞ ምህረተአብ የአጠቃላይ የድርጅቱ የኢንፎርሜሽን ዋና ሀላፊ ሆኖ መሾሙን ሰራተኖች ይገልጻሉ።
የትግራይ ተማሪዎች እንደማንኛውም ሰው በችሎታቸው ተወዳድረው ቢገቡ ክፋት አልነበረውም የሚሉት ሰራተኞች፣ የቅጥርም ሆነ የሹመት አሰጣጡ በዘረኝነት ላይ ተመስርቶ መሰጠቱ ለአገሪቱም ለተቀጣሪዎቹም መልካም አይደለም ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
ሰራተኞች በተለያዩ የአየር መንገዱ ክፍሎች የሚገኙ የሃላፊነት ቦታዎችም በተመሳሳይ መንገድ በአንድ ብሄር ሰዎች እየተያዙ መመጣታቸውን ይናገራሉ።
አንዳንድ ታዛቢዎች እንደሚሉት ከመከላከያ፣ ከደህንነትና ከፖሊስ በመቀጠል አየር መንገዱ የህወሃት አባላት በብዛት የሚሰባሰቡበት ቦታ ሆኗል። መንግስት ከዚህ ቀደም በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ሲነሳበት የቆየውን ክስ ፣ ከልምድ ጋር በማያያዝ ለመከለከል ሙከራ ሲያደርግ ቢቆይም፣ ከአየር መንግድ ጋር በተያያዘ ለሚቀርብበት የዘረኝነት ክስ ምላሽ አልሰጠም። አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በመንግስት ወጪ ወደ ውጭ አገር ለትምህርት ከሚላኩት መካካል ከ80 እስከ 90 በመቶ የሚሆኑት የዚህ ብሄር ተወላጆች ናቸው።
በአየር መንገዱ ውስጥ ስለሚታየው ዘረኝነት የድርጅቱን ሃላፊዎች ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም።