ኢሳት (ግንቦት 30 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ላይ ቅሬታን ማቅረብ የጀመሩ አንጋፋ የኢትዮጵያ አትሌቶች ፌዴሬሽኑ ባለሙያ የሚመራ አይደለም በማለት ፌዴሬሽኑ ሃላፊነቱን ለአትሌቶች እንዲያስረክብ ማክሰኞ ጠየቁ።
በወቅታዊ የሃገሪቱ የስፖርት ጉዳዮች ላይ በመምከር አስቸኳይ ምክክርን ያደረጉ አትሌቶች፣ ፌዴሬሽኑ ከአትሌቲክስ ዘርፍ ግንኙነት በሌላቸው አካላት በመመራቱ ቅሬታዎች እንዲበራከቱና በአትሌቲክስ ውድድርም ውጤት እየተመናመነ እንዲሄድ ማድረጉን ገልጸዋል።
ሰሞኑን ሃገሪቱን በብራዚሉ ኦሎምፒክ ላይ የሚሳተፉ አትሌቶችን ለመምረጥ በተካሄደው ሂደት ከአትሌቶች የተነሳው ቅሬታና ተቃውሞ የዚሁ ማሳያ መሆኑን የአትሌቶቹን ማህበርን በመወከል አትሌት ገብረእግዚያብሄር ገብርማሪያም ለሃገር ውስጥ ጋዜጠኞች አስታውቋል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ባለሙያዎች እየተመራ አይደለም ሲል የገለጸው አትሌቱ፣ የአትሌቶች ማህበር ፌዴሬሽኑ ሙሉ ስልጣኑን ለአትሌት ተወካዮች እንዲያስረክብ በማህበሩ አባላት በኩል ስምምነት መደረሱን አመልክቷል።
የአትሌቶች ማህበር ተወካዮች በፌዴሬሽኑ ስር ተወካዮችን እንዲወክል ቢያደርግም ፌዴሬሽኑ በአባላቱ ላይ የፈለገውን እርምጃ ሲወስድ መቆየቱን አንጋፋ አትሌቱ አክሎ ገልጿል።
ፌዴሬሽኑ ሃላፊነቱን ለአትሌቶች ለማስረከብ ፈቃደኛ ካልሆነ መንግስት በጉዳዩ ጣልቃ በመግባት የሽምግልና (የማደራደር) ስራ እንደሚገባ አትሌቱ በማህበሩ በኩል የተወሰዱ ውሳኔዎችን ዋቢ በማድረግ ለመገኛኛ ብዙሃን አስረድቷል።
አትሌት ቀነኒሳ በቀለን ጨምሮ በርካታ አንጋፋ አትሌቶች ፌደሬሽኑ በባለሙያ እየተመራ አይደለም በማለት ቅሬታ ማቅረብ መጀመራቸው ይታወሳል።
በተለይ ካለፈው ሳምንት ጅምሮ በመካሄድ ላይ ያለው የብራዚል ኦሎምፒክ ተሳታፊዎች ምርጫ በፌዴሬሽኑ ላይ ተቃውሞ እንዲቀሰቀስ ምክንያት መሆኑን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
አትሌቶቹ እያነሱ ያሏቸውን ጥያቄዎችን የሚከታተልና 10 አንጋፋ አትሌቶችን የያዘ ኮሚቴ የተቋቋመ ሲሆን አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ፣ አትሌት ቀነኒሳ በቀለ፣ ገብረእግዚያብሄር ገብረማሪያ እና ሌሎች አትሌቶች በኮሚቴው ተካተዋል።
ፌዴሬሽኑ አትሌቶችን ለመምረጥ እየተከትለ ያለው አካሄድ ሙያዊ አይደለም፣ እንዲሁም ሃገርን ሳይሆን ግለሰቦችን ለመጥቀም ያለመ ነው ሲሉ አትሌቶቹ ቅሪታን እያቀረቡ ይገኛሉ።
አሁን ባለው የአትሌቶች ማህበር አመራር ላይ ቅሬታ እንዳላቸው የገለጹት አትሌቶቹ ማህበሩ አስቸኳይ ስብሰባን እንዲያካሄድ በአትሌቶቹ ጥያቄ ቢቀርብለትም ምላሽ ሳይሰጥ መቅረቱን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
ማህበሩን እየመሩ ያሉ ተወካይ አትሌቶች በማክሰኞ ምክክር ላይ ባለመገኘታቸው ምክንያት ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል።