ኢሳት (ሚያዚያ 27 ፥ 2016)
ከ20 የሚበልጡ ታንኮችን የያዙ የኢትዮጵያ ወታደሮች ታፍነው የተወሰዱ ህጻናትን ለማፈላለግ በሚል ወደ ደቡብ ሱዳን መግባታቸውን የደቡብ ሱዳን መገናኛ ብዙሃን ረቡዕ ዘገቡ።
ማክሰኞ ፖቦር በሚሰኝ ስፍራ የታዩት እነዚሁ የኢትዮፕያ ወታደሮች ከባድ መሳሪያዎችን እንደታጠቁና ከጋምቤላ ክልል በኩልም የጦር ጀቶችን ወደ ስፍራው ሲበሩ መታየታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
የቦማ ግዛት አስተዳዳሪዎች በበኩላቸው በግዛቲቱ በሚገኙ ሶስት ቦታዎች የኢትዮጵያ ወታደሮች እንቅስቃሴ እያደረጉ ስለመሆናቸው በጁባ መንግስት መረጃ እንደተሰጣቸውም ገልጸዋል።
ከባድ መሳሪያን ታጥቀዋል የተባሉትና የደቡብ ሱዳንን ድንበር ዘልቀው ገብተዋል የተባሉት የኢትዮጵያ ወታደሮች በግዛቲቱ ጀበል ራድ፣ አኮቦ እና ፓቻላ ተብለው በሚጠሩ ስፍራዎች መሆናቸውን የቦማ ግዛት አስተባባሪ ጋብሬል አሞኮሪ ለሱዳን ትሪቢዩን ጋዜጣ አስረድተዋል።
የቦማ ግዛት የማስታወቂያ ሚኒስትር የሆኑት ጁሊየስ ጀምስ አቶንግ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ወታደሮች ወደግዛቲቱ ስለመግባታቸው መረጃ ቢደርሳቸው ረቡዕ ድረስ የት እንዳሉ እንደማያውቁ ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
ሚኒስትሩ ከቀናት በፊት ተጠለው ተገኝተዋል የተባሉ 32 ህጻናትም አሁንም ድረስ ሲኳንጎል ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በሚገኙና ለተባበሩት መንግስታት ተሰጥተው ወደሃገራቸው የሚገቡበት ሁኔታ እንደሚመቻች ለጋዜጣው ገልጸዋል።
በአካባቢው ተጨማሪ ህጻናትን የማፈላለጉ ስራ ቀጥሎ እንደሚገኝ የተናገሩት ሚኒስትሩ ጁሊየስ ኦቶንግ ሌሎች ህጻናትም ይገኛሉ የሚል ተስፋ መሆንሩንም አስታውቀዋል።
ህጻናቱ ይገኙበታል በተባለው አካባቢ የሚኖሩ የጎሳ መረጃዎች ከግዛቲቱ ባለስልጣናት ጋር ምክክርን እያካሄዱ እንደሆነም ታውቋል።