ኢሳት (ሰኔ 7 ፥ 2008)
ለሶስት መንግታዊ ተቋማት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ አገልግሎት ሲሰጥ የነበረ የመዳብ የኤሌክትሪክ ገመድ ማንነታቸው ባልታወቁ አካላት መዘረፉን ተከትሎ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በአለም አቀፍ ደረጃ የሚያካሄደው የንግድ አገልግሎት ተስተጓጎለ።
ከሁለት ሳምንት በፊት ተፈጽሟል በተባለው የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያው መስመር መዘረፍ ምክንያት የኢትዮጵያ ምርት ገበያን ጨምሮ የኢትዮጵያን የዱር አራዊት ጥበቃ ባለስልጣን ስራቸው ማካሄድ እንዳልቻለ ታውቋል።
ፖሊስ ከ10 ሜትር በላይ የሚሆነው የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ከህንጻዎቹ ቅጥር ግቢ በማን ዝርፊያ እንደተፈጸመበት ለማወቅ ምርመራን እያካሄደ ሲሆን፣ ለመንግስታዊ ተቋማቱ የጥበቃን አገልግሎት የሚሰጠው ድርጅት ገመዱን የመጠበቁ ሃላፊነት በድርጅቱ ስር እንዳልተካተተ ምላሽ መስጠቱን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይልን የሚያስተላልፈው ገመድ ከስምንት አመት በፊት የተዘረጋና 15ሺ ቦልት የመሸከም አቅም እንደነበረው ለመረዳት ተችሏል።
በሶስቱ ድርጅቶች ላይ የተፈጸመውን ይህንኑ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ገመድ ድርጊት ተከትሎ በከተማዋ የሚገኙት ፍልውሃ፣ ፒያሳና ሜክሲኮ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቋረጡን ከሃገር ቤት ከተገኘው መረጃ ለመረዳት ተችሏል።
ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ማስተላለፊያ ገመዱ የግንቦት 20 በዓል አካባበር በዋዜማው በድርጅቶቹ ሰራተኞች ተከብሮ ከዋለ በኋላ መፈጸሙ ታውቋል።
ለቀናት ያህል ስራው ተስተጓጉሎ የቆየው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ የጄኔሬተር አገልግሎትን በጊዜያዊነት ስራ ላይ ያዋለ ሲሆን፣ በሶስቱ መንግስታዊ ድርጅቶች ውስት የሚሰሩ በርካታ ሰራተኞች ችግሩ ዕልባት እስኪያገኝ ድረስ ስራ እንዳይገቡ እንደተነገራቸው ለመረዳት ተችሏል።
ምርመራ እያካሄደ የሚገኘው ፖሊስ በበኩሉ ጉዳዩን በመከታተል ላይ በመሆኑ ዝርዝር መረጃን እንደማይሰጥ አስታዉቋል።
የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ድርጁት በአማራጭነት የጄኔሬተር አገልግሎትን ስራ ላይ ለማዋል የ15ሺ ብር የተጨማሪ በጀት መጠየቁንና የ10ሺ ብር ክፍያ መፈጸሙ ታውቋል።
የተቀሩት ሁለቱ መንግስታዊ ድርጅቶች ለሁለተኛ ሳምንት ጊዜ ስራቸው ሙሉ ለሙሉ ተስተጓጉሎ መቀጠሉን ከሃገር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።