የኢትዮጵያ መጻኢ እድል አስፈሪ ነው ሲል ዘኢኮኖሚስት መጽሄት ዘገበ

ጥቅምት ፬ (አራት) ቀን ፳፻ / ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱንና አሳሳቢ አስከፊ ደረጃ ላይ መድረሱን ዘ ኢኮኖሚስት መጽሄት ኢትዮጵያ ላይ አትኩሮ በሰራው  የፖለቲካ እና ምጣኔ ሃብታዊ ዳሰሳ አመልክቷል።

በቢሾፍቱ ከተማ ኢሬቻ የምስጋና በዓል ለማክበር በተሰበሰቡት ንፁሀን ዜጎች ላይ የደረሰውን እልቂት “አሰቃቂ” በማለት የዘገበው ዘ ኢኮኖሚስት፣ ከዚህ አሰቃቂ እልቂት በኋላ በኢትዮጵያ አስቸኳይ የጊዜ አዋጅ መታወጁን ፣ ንብረትነታቸው የእስራኤል፣ የቱርክ እና የአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ ውድመት መድረሱን እንዲሁም አንዲት አሜሪካዊት ዜጋ ሕይወቷ ማለፉን አስታውሷል።

ሕዝባዊው አመፅ ከተነሳበት ካለፈው አመት ጀምሮ ከ500  በላይ የሚሆኑ ንፁሃን ዜጎች በመንግስት ታጣቂዎች በግፍ ተገለዋል። ገዥው ህወሃት ኢህአዴግ በአሁኑ ወቅት ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ሲበረቱበት ዋና ከተማዋን አዲስ አበባን ጨምሮ በመላው አገሪቷ የኢንተርኔት አገልግሎትን እንዲቋረጥ ማድረጉንም ጠቅሷል።

በአገርቷ በሚታየው ኢፍትሀዊ አገዛዝ አብዛኛው ሕዝብ ደስተኛ አለመሆኑን እና አብዛኛው ሕዝብ መሬቱ እና ንብረቱን ከሕግ አግባብ ውጪ በመንግስት መነጠቁን፣ ከኢትዮጵያ ሕዝብ 6 በመቶ ብቻ የሆኑት አናሳዎቹ የትግራይ ብሄር ተወላጆች ብዙሃንን ባገለለ ሁኔታ የሃብት እና የስልጣን ክፍፍሉን ብቻቸውን በበላይነት መቆጣጠራቸውን መጽሄቱ አስነብቧል።

ይህም ኢፍትሃዊ የስልጣን ክፍፍል በሀገሪቷ ለተነሳው ሕዝባዊ ተቋውሞዎች አንዱ መንስኤ በመሆን ለተቃውሞዎች መባባስ ከፍተኛውን ድርሻ ወስዷል።በመንግስት ላይ ቁጣቸውን እየገለፁ ያሉት አርሶ አደሮች ወደ ሀገሪቷ ርእሰ ከተማ የሚገቡ እቃዎችን ማስተጓጎላቸውቸውንና በሀገሪቷ ያሉ የተቋዋሚ አመራሮች የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ በተቃውሞዎቻቸው አስተጋብተዋል።

ከ193  በላይ ሰላማዊ ዜጎች ካለቁበት ከምርጫ 1997 ዓ.ም በኋላ ከፍተኛ የሆነ ሕዝባዊ እንቢተኝነት ለመጀመሪያ ጊዜ ተከስቷል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ወቅታዊ ጥያቄዎች የመንግስት ተሃድሶዋዊ ለውጥን ሳይሆን ስርነቀል የስርዓት ለውጥ መሆኑን  ዘ ኢኮኖሚስት ዘግቧል።

በተመሳሳይ ዜና በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ የሆላንድ ድርጅቶች በአገሪቱ አድማሱን በማስፋት በተቀጣጠለው ሕዝባዊ እንቢተኝነት ምክንያት ማሳዎቻቸው በእሳት መጋየታቸው እና የንብረት ውድመት መድረሱን ተከትሎ ወደ ውጪ ይልኩት የነበረውን የግብርና ምርቶች ለማቆም ተገደዋል። ከምርት ማቆሙ ጋር በተያያዘ የተፈጠረውን አቅርቦት ጉድለት ለሞሙላት ፊታቸውን  ወደ ኬኒያ እና ዝምባቡዌ አዙረዋል።

ከሕዝባዊ እምቢተኝነቱ ጋር በተያያዘ በኢትዮጵያ የግብርና ምርቶች ላይ ተሰማርተው የነበሩት የውጪ ኩባንያዎች በተለይም የኔዘርላንድስ ኩባንያዎች ምርት ማምረታቸውን ማቆማቸውን ተከትሎ፣  በኩባንያዎቹ የአክስዮን ገበያ ላይም ሆነ በምርቶቹ ዋጋ ላይ ጭማሪ ይኖራል የሚል ስጋት መኖሩን እና ይህንንም ስጋት ለመቅረፍ ኩባንያው ፊቱን ወደ ኬንያ፣ ዚምባቡዌና ጓቲማላ ማዞሩን ግሎባል ቤሪ ኮንግረስ ዘግቧል፡፡

በሌላ በኩል ገዢው ፓርቲ የጣላቸውን እገዳዎች በአፋጣኝ በማንሳት የሰብዓዊ መብቶችን ካለምንም ገደብ እንዲያከብር  የካናዳ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር  ስቴፋኒ ዲዮን ጠየቁ።

ለተከታታይ ስድስት ወራት የሚዘልቀውን አስቸኳይ የጊዜ አዋጅን በማንሳት የጸጥታ ኃይሎች ከሚወስዷቸው የሃይል እርምጃዎች እንዲታቀቡ እንዲሁም ካለምንም ቅድመ ሁኔታዎች ሁሉንም መሰረታዊ የሆኑ የሰብዓዊ መብቶችን እና ነጻነቶችን ማክበር ሊያከብር ይገበዋል ሲሉ አሳስበዋል።

ሁሉንም ኢትዮጵያዊያን ዜጎች ባሳተፈ መልኩ የአገሪቱን ዴሞክራሲያዊ  ሽግግር ስርዓት ለመቀየር አጠቃላይ ውይይት መደረግ እንዳለበት የካናዳ መንግስት እምነት መሆኑንም ሚንስትሩ ገልጸዋል።