የኢትዮጵያ መንግስት ግድያውን አስመልክቶ የተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ያቀረበውን የማጣራት ጥያቄ እንደማይቀበል ገለጸ

ኢሳት ( ነሃሴ 5 ፥ 2008)

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በኢትዮጵያ እየተፈጸመ ያለው ግድያ በአለም አቀፍ ገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበት ሲል ያቀረበን ጥያቄ የኢትዮጵያ መንግስት ፈቃደኛ እንደማይሆን ሃሙስ አስታወቀ።

የሰብዓዊ መብት ኮሚሽኑ ረቡዕ ባስተላለፈው ጥሪ የኢትዮጵያ መንግስት ለአለም አቀፍ መርማሪ አካል በሩን ክፍት እንዲያደርግ ከዋና መስሪያ ቤቱ ስዊዘርላንድ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።

ይሁንና ለተባበሩት መንግስታት ጥሪ ምላሽን የሰጠው የኢትዮጵያ መንግስት ግድያውን እንዲያጠራ ወደ ሃገሪቱ እንዲገቡ የተፈለገ አካልን እንደማይቀበል ምላሽን ሰጥቷል።

የመንግስት ቃለ አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ በሃገሪቱ በርካታ የተባበሩት መንግስታት አካላት ያሉ በመሆኑን መርማሪ ቡድኑ መላኩ አስፈላጊ አይደለም ሲሉ ለአልጀዚራ ቴሌቪዥን ጣቢያ አስታውቀዋል።

ይሁንና በሃገሪቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቅርንጫች ተቋማት እንጂ የተፈጸመ ግድያን የሚያጣራ አካል አለመኖሩን የተመድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ረቡዕ በሰጠው መግለጫ አመልክቷል።

ድርጅቱ የተፈጸመውን ግድያ ለማጣራት የተጠየቀውን ጥያቄ ውድቅ ያደረገው የኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ሃይሎች ከመጠን ያለፈ የሃይል ዕርምጃ ለመመውሰዱ የራሱን ምርመራ ያካሂዳል ሲሉ ገልጿል።

ይሁንና ምርመራው መቼ እንደሚካሄድና መንግስት የሰጠው ዝርዝር መረጃ የሌለ ሲሆን ህዝባዊ ተቃውሞው መቀመጫቸውን በውጭ ባደረጉ አካላት የተፈጸመ ነው ሲል ምላሽ መስጠቱን አልጀዚራ በዘገባው አመልክቷል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሃላፊ የሆኑት ዘይድ ራድ አል ሁሴን በሳምንቱ መገባደጃ ላይ ከ100 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው የመንግስት እርምጃ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ለአለም አቀፉ መገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

በኦሮሚያ ክልል ለወራት ዘልቆ የቆየውና ከ400 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው ግድያ ምንም ምርመራ እንዳልተካሄደበት ያወሱት ሃላፊው በሰላማዊ ሰዎች ላይ እየተወሰደ ያለው ግድያና የጅምላ እስራት አለም አቀፍ አጀንዳ እየሆነ መምጣቱን አክለው ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል በመንግስት የተፈጸሙ ግድያዎችን በተመለከተ ሂውማን ራይትስ ዎች ከ400 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ያሰባሰበውን መረጃ ዋቢ በማድረግ በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ግድያ ከተፈጸመባቸው ነዋሪዎች በተጨማሪ በ10ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በተለያዩ እስር ቤቶችና ወታደራዊ ማሰልጠኛ ተቋማት ውስጥ ለእስር ተዳርገው እንደሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ይገልጻል።