ጥር ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፮ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የግብጽ ባለስልጣናት የአባይን ግድብ በተመለከተ ከኢትዮጵያና ሱዳን ጋር ሲያደርጉት የነበረውን ድርድር ካቋረጡ በሁዋላ ጉዳዩን ወደ ተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ሌሎች ለጋሽ አጋራት ለመውሰድ መወሰናቸውን የግብጽ ባለስልጣኖች መናገራቸውን ተከትሎ ግብጽ በየትኛውም መድረክ ብትሄድ ምንም የምታመጣው ነገር እንደሌለ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት እየተናገሩ ነው።
አንዳንድ የመገናኛ ብዙሀን የመንግስትን ባለስልጣናት በመጥቀስ ግብጽ የአባይን ግድብ ግንባታ ለማስቆም የህግ ድጋፍ እንደሌላት ሲገልጹ፣ ግብጽ በበኩሉዋ በቅኝ ግዛት ጊዜ የነበሩ ውሎች እንዲከበሩላት እንደምታነሳ ጠቁመዋል።
ግብጽ የዲፕሎማሲ ዘመቻ በመጀመር ለኢትዮጵያ ምንም አይነት የውጭ ድጋፍ እንዳይደረግ ለጋሽ አገራቱን ለማሳመን ትጥራለች። አገሪቱ በዲፐሎማሲው ረገድ ካልተሳካላት በሂደት ስለምትወስደው እርምጃ ግልጽ የሆነ ነገር የለም።
ሁለቱ አገራት በግድቡ ምክንያት በቀጥታ ወደ ግጭት ካመሩ፣ ከ150 አመታት በሁዋላ የተካሄደ ጦርነት ይሆናል። ግብጾች በአጼ ዮሀንስ ዘመን ያካሄዱት ተደጋጋሚ ወረራ በኢትዮጵያ የበላይነት ተጠናቋል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ግብጾች የመንግስትን ተቃዋሚዎች በማስታጠቅ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ ተዘዋዋሪ ሚና ሲጫወቱ ቆይተዋል።