ኢሳት (ታህሳስ 6 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ መንግስት ዲፕ ፓኬት ኢንስፔክሽን (Deep Packet Inspection) የተሰኘና የኢንተርኔት የስለላ ተግባርን ለማከናወን የሚረዳ ቴክኖሎጂን እየተጠቀመ እንደሚገኝ ተገለጸ።
ቴክኖሎጂው በህጋዊ መንገድ የደህንነት ተያያዥ ስራዎችን ለማከናወን በተለያዩ አለም አቀፍ ኩባንያዎች በመቅረብ ላይ ቢሆንም፣ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሃገራት አገልግሎቱን እየገዙ ለኢንተርኔት የስለላና ቁጥጥር ስር በማዋል መሆናቸውን አምነስቲ ኢንተርናሽናል መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ይፋ አድርጓል።
ቴክኖሎጂውን ለስለላ ተግባር እየተጠቀመ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግስት ለህዝብ የታገዱ ድረ-ገጾችን ለመከታተል እንዲሁም የኢንተርኔት አገልግሎት ተጠቃሚዎች በኢሜይልና በቀጥታ የመልዕክት (ቻት) ልውውጥ የሚያደርጉትን መረጃ ለመከታተል ማዋሉን የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አስታውቋል።
የቴክኖሎጂውን አገልግሎት ያለው ፍላጎት መጨመርን ተከትሎ የዚሁ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የገበያ ድርሻ በቀጣዮቹ ሶስት አመታት ውስጥ ወደ 5 ቢሊዮን ዶላር እንደሚደርስ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይኸው ዲፕ ፓኬት ኢንስፔክሽን የተሰኘው የቴክኖሎጂ አገልግሎት በተለይ በሞባይል የእጅ ስልኮች ላይ ያሉ መረጃዎችን በቀላሉ መንገድ ለመከታተልና ለመቆጣጠር እንደሚረዳ በጉዳዩ ዙሪያ ከተጻፉ መረጃዎች ለመረዳት ተችሏል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ እያደረገች ያለውን የኢንተርኔት አፈናና ቁጥጥር ለመረዳት ኦፕን ኦብዘርባቶሪ ኦፍ ኔት ዎርክ ከተሰኘ ኩባንያ ጋር አምስት ወር የፈጀ ጥናት ማካሄዱን አፍሪካ ኒውስ መጽሄት ሃሙስ ዘግቧል።
የጥናቱ ግኝት ሰሞኑን ይፋ ያደረገው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ኢትዮጵያ በሃገሪቱ የተቀሰቀሰን ህዝባዊ ተቃውሞ ለመቆጣጠር ሲል 16 ድረገጾችን ዝግ አድርጎ መቆየቱን አስታውቋል።
ድርጊቱ ህጋዊ መሰረት እንደሌለው የሚገልጸው አምነስቲ ኢንተርናሽናል መንግስት አገልግሎቱን ከሟቋረጥ ይልቅ ከህዝቡ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ ቢሰጥ የተሻለ እንደሚሆን ገልጿል።
በኢትዮጵያ የስልክ መሰረተ ልማት በማስፋፋት ላይ የሚገኘው ህአዌ ቴክኖሎጂን ጨምሮ ኖኪያ፣ አልካቴል፣ ኤሪክሰን እና ሲስኮም ሲስተም የተሰኙ 19 የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች የዲፕ ፓኬት እንስፔክሽን አቅራቢዎች መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።
የቻይናው ሁአዌ ቴክኖሎጂ ከጥቂት ከጥቂት አመታት በፊት የራሱን ብድር በማቅረብ በኢትዮጵያ ከሁለት ቢሊዮን ዶላር የሚፈጀው የስልክ መሰረተ ልማት ለማካሄድ ከመንግስት ጋር ስምምነት መፈጸሙ ይታወሳል።
ከአንድ አመት በፊት ገዢው የኢህአዴግ መንግስት ከአንድ የጣሊያን ቴክኖሎጂ ኩባንያ ጋር አንድ ሚሊዮን ዩሮ የሚበልጥ ስምምነት በመፈጸም የኢንተርኔት ቁሳቁስ ሲገዛ መቆየቱ መጋለጡ ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣና ሌሎች አለም አቀፍ መገናኛ ብዙርሃን ሰፊ ስፋን ሲሰጡ ቆይተዋል።
የዚሁ የስለላ ተግባር ተጎጂ የሆነ አንድ ትውልደ ኢትዩጵያዊ አሜሪካዊ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ክስን አቅርቡ ጉዳዩ በሂደት ላይ መሆኑም ታውቋል።