የኢትዮጵያ መንግስት የተመድና የአውሮፓ ህብረት በአገሪቱ የተፈጸሙ ግድያዎችን ለማጣራት ያቀረበውን ጥያቄ እንደማይቀበል አስታወቀ

ኢሳት (ሚያዚያ 10 ፥ 2009)

የኢትዮጵያ መንግስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአውሮፓ ህብረት በመቶዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ምክንያት የሆነውን ግድያ ለማጣራት ያቀረቡትን ጥያቄ እንደማይቀበል በይፋ ምላሽ ሰጠ።

ሁለቱ አለም አቀፍ ተቋማት ባለፈው አመት በኦሮሚያ ክልል ተቀስቅሶ ከነበረው ህዝባዊ ተቃውሞ ጋር በተገናኘ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የሃይል ዕርምጃ በመውሰድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸማቸውን ሲገልጹ ቆየተዋል።

ይኸው የጸጥታ ሃይሎች ግድያና የሰብዓዊ መብት ጥሰት በገለልተኛ አካል ምርመራ እንዲካሄድበትና ድርጊቱን የፈጸሙ አካላት ለፍትህ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።

ይሁንና ከቢቢሲ ጋር ቃለምልልስን ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ መንግስት ከተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ከአውሮፓ ህብረት የቀረበውን የምርመራ ጥያቄ እንደማይቀበለው አስታውቀዋል።

መንግስታዊው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጉዳዩን በቸልተኝነት የሚመረምር አካል ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የመንግስታቸውን አቋም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮሚሽኑ ገለልተኛ ነው ቢሉም አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በመንግስት የሚካሄደው ምርመራ ነጻና ገለልተኛ እንደማይሆን ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛል።

የአለም አቀፉ ማህብረሰብ ጥያቄን እንደማይቀበሉ የተናገሩት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ የሃገሪቱ ሉዓላዊነት መከበር ይኖርበታል ሲሉ በቃለ-ምልልሳቸው አስረድተዋል።

ለአንድ አመት ያህል በኦሮሚያ ክልል የዘለቀውን ህዝባዊ ተቃውሞ ተከትሎ ከ700 የሚበልጡ ሰዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች መገደላቸውን ሂውማን ራይስት ዎችና ሌሎች የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ሲገልጹ መቆየታቸው ይታወሳል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሃላፊ የሆኑት ዘይድ ራድ አል ሁሴን የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በኦሮሚያና አማራ ክልሎች በሰልፈኞች ላይ ቀጥተኛ የተኩስ ዕርምጃ መውሰዳቸውን በቅርቡ አመልክተዋል።

በወቅታዊ የሃገሪቱ ጉዳዮች ዙሪያ ከቢቢሲ ጋር ቃለምልልስን ያደረጉት አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በቅርቡ ለአራት ወር እንዲራዘም የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጋጋትን እያመጣ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ይሁንና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም ድረስ በእስር ላይ እንደሚገኙና ለህግ እንደሚቀርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አተገባበር የሚከታተለው ኮማንድ ፖስት ወደ አምስት ሺ የሚጠጉ ሰዎች ከህዝባዊ ተቃውሞው ጋር በተገናኘ በቅርቡ ክስ እንደሚመሰረትባቸው ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

አሁንም ድረስ በአንዳንድ የሃገሪቱ አካባቢዎች አለመረጋጋት በመኖሩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲራዘም መደረጉን ኮማንድ ፖስት አመልክቷል።