የኢትዮጵያ መንግስት የበርበራን ወደብ በዘቂላነት ለመጠቀም ከሶማሊላንድ ጋር እየተደራደረ ነው

ኢሳት (መጋቢት 27 ፥ 2008)

የኢትዮጵያ መንግስት ራሷን ነጻ ሃገር አድርጋ ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር ዘላቂ የወደብ አገልግሎትን ለማግኘት በክፍያ ዙሪያ ድርድር ጀመረ።

በማንም ሃገር እውቅናን ያላገኘችው ሃገሪቱ በየአመቱ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላርን እንደምታገኝና ገቢውም የሶማሊላንድ ኢኮኖሚ ለማገዝ እንደሚጠቅም ባለስልጣናት ገልጸዋል።

በጅቡቲ ወደብ በተደጋጋሚ ሲደረግባት የቆየን የአገልግሎት ክፍያን ጭማሪ ተከትሎ ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን ለመጠቀም ለአመታት ድርድርን ስታደርግ መቆየቷንም ማርግ የተሰኘ የሶማሊላንድ ጋዜጣ ማክሰኞ ዘግቧል።

በቅርቡ በጅቡቲ ወደብ የተፈጠረውን መጨናነቅ ምክንያት በማድረግ የመንግስት ባለስልጣናት የበርበራ ወደብን በአስቸኳይ ለመጠቀም መወሰናቸውም ታውቋል።

የሁለቱ ሃገራት ተወካዮችም በሳምንቱ መገባደጃ የበርበራ ወደብን ለመጠቀም ስምምነት እንደፈጸሙ የዘገበው ብሉምበርግ የዜና ወኪል በክፍያ አገልግሎት ዙሪያም ማሻሻያዎች መደረጋቸውን አመልክቷል።

ይሁንና ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን በቋሚነት ለመጠቀም ስምምነት ብትፈጽምም፣ የአገልግሎቱ ክፍያ ግን ይፋ አልተደረገም።

ላለፉት በርካታ አመታት የጅቡቲ ወደብን በብቸኝነት ስትጠቀም የቆየችው ኢትዮጵያ፣ በየአመቱ ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ለወደብ አገልግሎት እየከፈለች እንደምትገኝ ታውቋል።

በየጊዜው የጅቡቲ ወደብን በሚያስተዳድሩ አካላት የሚደረገው የዋጋ ጭማሪም በኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩም ይነገራል።

በኢትዮጵያ ድንበር 200 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የበርበራ ወደብ በቂ መሰረተ-ልማቶች ያልተሟሉለት ሲሆን ራሷን ሃገር አድርጋ ያወጀችው ሶማሊላንድ ከአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና አለማግኘቷም ተፅዕኖ ማሳደሩ ተነግሯል።

ኢትዮጵያ 30 በመቶ የሚሆነውን የንግድ ልውወጥ በበርበራ ወደብ ለማድረግ ፍላጎት ያላት ቢሆንም ወደቡ ምን ያህል መርከቦችን የማስተናገድ አቅም እንዳለው አለመታወቁን ብሉምበርግ በዘገባው አመልክቷ።