ኢሳት (ሚያዚያ 12 ፥ 2008)
በተያዘው አመት ስኳርን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እቅድ ይዞ የነበረው መንግስት የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ሊጠናቀቅ ባለመቻሉ እቅዱ ለሁለተኛ ጊዜ መስተጓጎሉን የስኳር ኮርፖሬሽን ገለጠ።
መንግስት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብን በመመደብ አራት የስኳር ፋብሪካዎችን ስራ ለማስጀመር ጥረት ቢያደርግም ፋብሪካዎቹ መጠናቀቅ እንዳልቻሉ ታውቋል።
በሃገሪቱ በመባባስ ላይ ያለው የድርቅ አደጋ በነባር የስኳር ፋብሪካዎች ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩንና ስኳርን ከውጭ ሃገር ለማስገባት ውሳኔ መድረሱን የስኳር ኮርፖሬሽን ይፋ አድርጓል።
የአዲስ ፋብሪካዎች ግንባታዎች ለመጠናቀቅ እና በነባር ፋብሪካዎች ላይ የደረሰውን የድርቅ አደጋ ተፅዕኖ ተከትሎም መንግስት ከ2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስኳርን ከውጭ ለማስገባት መገደዱ ኮርፖሬሽኑ ገልጿል።
ባለፈው አመት መንግስት የስኳር ምርትን ወደ ውጭ ለመላክ እቅድ ይዞ የነበረ ቢሆንም፣ እቅዱ ሊሳካ አለመቻሉን የስኳር ኮርፖሬሽን ባለስልጣናት ማስታወቃቸው ይታወሳል።
ይህንኑ እቅድ በተያዘው አመትም ለማሳካትም የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቢቆይም የአዲስ አበባ የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሊደርስ አለመቻሉን የኮርፖሬሽኑ ስራ አስፈጻሚ አቶ ጋሻው አይችሉህም ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።
የህንድ መንግስት ለአዳዲሶቹ የስኳር ፋብሪካዎች ግንባታ ከጥቂት አመታት በፊት የ600 ሚሊዮን ዶላር ብድርን ሰጥቶ የነበረ ሲሆን መንግስት ከተለያዩ የገንዘብ ተቋማት የብሄራዊ ባንክ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለዚሁ ፕሮጄክት መመደቡ ታውቋል።
ይሁንና፣ ቀድሞ በአባይ ጸሃየ ስር ይተዳደር የነበረው የስኳር ኮርፖሬሽን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ኪሳራ ደርሶበት እንደነበር የኢቶፕያ ልማት ባንክ ምንጮች ከወራት በፊት ለኢሳት መግለጻቸው ይታወሳል።
ለፋብሪካዎቹ ግንባታ የሚሰጠው ግልጽ ያልሆነ ጨረታና ለእቃ ግዢዎች የሚወጡ በጀቶች በስኳር ኮርፖሬሽኑ ላይ የገንዘብ ኪሳራ ማስከተሉንም እነዚሁ ምንጮች አስረድተዋል።
በአሁኑ ሰዓት ነባሮቹ የስኳር ፋብሪካዎች በአመት አራት ሚሊዮን ኩንታል ስኳርን እያመረቱ ሲሆን የሃገሪቱ የስኳር ፍላጎት ግን በአመት ከስድስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ መሆኑንም ለመረዳት ተችሏል።