ኢሳት (ሃምሌ 13 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ መንግስት ያጋጠመውን የውጭ ምንዛሪና የፋይናንስ እጥረት ተከትሎ ለአመታት ዝግ ሆነው የቆዩ የፋይናንስ ህጎችንና መመሪያዎችን በማሻሻል ላይ መሆኑን አለም አቀፍ የፋይናንስ አካላት አስታወቁ።
ሃገሪቱ መውሰድ የጀመረችውን እርምጃ እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ ኬኒያና የተለያዩ ሃገራት የፋይናንስ ተቋማትና ባንኮች በፋይናንስ አቅርቦት ላይ ለመሰማራት ድርድር እያካሄዱ መሆኑን ዘ ስታንዳርድ የተሰኘ የኬንያ ጋዜጣ ማክሰኞ ዘግቧል።
በኬንያ ብድርን በማቅረብ የሚታወቀው የኬንያው ኮ ኦፕሬቲቭ ባንክ ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ጊዲዮን ሙሪኡኪ የኢትዮጵያን መንግስት የፋይናንስ በሩን ለውጭ ኩባንያዎች ለመክፈት የወሰደውን እርምጃ በመጠቅም ኩባንያው በሃገሪቱ ቅርንጫፍ ባንክ ለመክፈት ዝግጅትና ድርድር እያደገ መሆኑን አስረድተዋል።
ከ90 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ኢትዮጵያ ከህዝቧ መካከል 15 በመቶ ብቻ የሚሆነው የባንክ አገልግሎት ያገኛል ያሉት ሃላፊው የፖሊሲ ማስተካከያው ተጠቃሚ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ለጋዜጣው ገልጸዋል።
ይሁንና የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች መንግስት በባንኮች ላይ የሚያደርገው ቁጥጥር ለውጭ ባንኮች ችግርን ሊፈጥር እንደሚችል በመግለጽ ላይ መሆናቸውን ዘስታንዳርድ ጋዜጣ በዘገባው አስፍሯል።
በምስራቅ አፍሪካ የፓይን ብሪጅ ኢንቨስትመንት ኦፊሰር የሆኑት ኒኮላስ ማላኪ የኬንያ የፋይናስ ተቋማት በቂ ጥናትንና ዝግጅትን ሳያደርጉ ወደ ኢትዮጵያ መግባት እንደሌላቸው ከጋዜጣው ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።
ሃገሪቱ በቅርቡ ተግባራዊ ማድረግ የጀመረችው የፋይናንስ ፖሊሲ ማሻሻያ በኢትዮጵያ ሁሉም ነገር ለውጭ ኩባንያዎች ክፍት ተደርጓል ማለት አይደለም ሲሉ ማላኪ አስታውቀዋል።
ይሁንና መንግስት የፋይናንስ እጥረት ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ በተለይ የውጭ ባንኮች በሃገሪቱ እንዲሰማሩ ፍላጎት መኖሩንና አጋጣሚው ለፋይናንስ ተቋማት ጥሩ ሊሆን እንደሚችል ሃላፊው አክለው አስረድተዋል።
የኢትዮጵያውያን የነፍስ ወከፍ ገቢ ወደ 550 ዶላር አካባቢ መሆኑን የገለጹት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው፣ አሃዙ በአህጉሪቱ ካለው አማካኝ 762 ዶላር ጋር ሲነጻጸር እጅግ አነስተኛ መሆኑንና ከፍተኛ ትርፍን ለሚጠብቁ ኩባንያዎች አመቺ ላይሆን እንደሚችል ከጋዜጣው ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያን ግማሽ ያህል ህዝብ ቁጥር ያላት ኬንያ ከ40 በላይ ባንኮች እንዳሏት ለመረዳት ተችሏል።