የኢትዮጵያ መንግስት ተመድ በአማራና ኦሮሚያ ለተፈጸሙት ግድያዎች የማጣራት ጥያቄ ይፋዊ የእምቢተኝነት ምላሽ ሰጠ

ኢሳት (ነሃሴ 13 ፥ 20108)

የኢትዮጵያ መንግስት ተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአማራና ኦሮሚያ ክልሎች የተፈጸሙ ግድያዎች በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ለቀረበለት ጥያቄ ተባባሪ እንደማይሆን ይፋዊ የጽሁፉ ምላሽን ሰጠ።

በክልሎቹ እየተካሄዱ ያሉ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን “ህገወጥና በሽብርተኛ ቡድኖች” የሚካሄዱ ናቸው ሲል በምላሹ ያሰፈረው መንግስት ከተቃውሞው ጋር በተገኛኘ የሞቱ ሰዎችን ጉዳት የደረሰባቸውን አካላት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ጋር በመተባበር የራሱን ማጣራት እንደሚያካሄድ አስታውቋል።

የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በሁለቱ ክልሎች የሃይል እርምጃዎችን እንደተፈጸሙ በመግለጽ አሳሳቢ ነው ሲል ያስታወቀው ድርጊት በአለም አቀፍ ገለልተኛ ቡድን ማጣራት እንዲካሄድበት ተጠያቂ መሆን ያለባቸው አካላት ለፍትህ እንዲቀርቡ ጥያቄ ማቅረቡ ይታወሳል።

ይሁንና ስዊዘርላን ጄኔቭ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኗሪ መልዕክተኛ በኩል ምላሽ የሰጠው መንግስት የቀረበለትን ጥያቄ ከመቀበል ይልቅ የራሱን ምርመራ እንደሚያካሄድ በጽሁፍ መልስ ገልጿል።

መንግስት ለተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በጻፈው በዚህ ባለሶስት ገጽ ምላሽ በክልሎች እየተካሄዱ ያሉ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ህገወጥና በሽብርተኛ ቡድኖች አነሳሽነት የሚካሄዱ ናቸው ሲል አመልክቷል።

እነዚህ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ህብረተሰቡን በዘርና በሃይማኖት በመከፋፈል ስልጣንን በህገወጥ መንገድ ለመያዝ ያለመ ነው ሲል መንግስት ለተባበሩት መንግስታት በሰጠው ምላሽ አክሎ ገልጿል።

በቅርቡ አደባባይ የወጡ የጎንደርና የባህር ዳር እንዲሁም በዙሪያዋ ያሉ ነዋሪዎች የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ህጋዊ ምላሽ እንዲያገኝና የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች በኦሮሚያ ክልል የሚፈጽሙትን ግድያ እንዲያቆሙ መጠየቃቸው ይታወሳል።

የመንግስት ባለስልጣናት ተቃውሞ በሽብርተኞች የተጠራ እንደሆነ በተደጋጋሚ ቢገልጹም ሰልፈኞቹ በመንግስት ባለስልጣናት ላይ ቅሬታን በማሰማት ተቃውሞን በሽብርተኛ መፈረጁ አግባብ እንዳልሆነ ሲቃወሙ ቆይተዋል።

መንግስት ህዝባዊ ተቃውሞ በሽብርተኛ ቡድኖች የተዘጋጀ ነው ሲል ምላሽን ቢሰጥም ድርጊቱን ለመመርመር በሚካሄደው ማጣራት ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቀጥታ ምክክርን እንደሚያካሄድ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሰጠው የጽሁፉ ምላሽ አመልክቷል።

መቀመጫውን በጄኔቭ ከተማ ያደረገው የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ለመንግስት ባለ ሁለት ገጽ ደብዳቤ በመጻፍ የኢትዮጵያ መንግስት ለቀረበው ጥያቄ በጎ ምላሽን እንዲሰጥ አሳስቧል።

ኮሚሽኑ ያቀረበውን ጥያቄ ተከትሎ ሂውማን ራይትስ ዎችና ሌሎች አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኢትዮጵያ የልማት አጋሮች የራሳቸውን ጫና በማሳደር የኢትዮጵያ መንግስት የቀረበለትን ጥያቄ እንዲቀበል ዘመቻን እያካሄዱ ይገኛል።