የኢትዮጵያ መንግስት በጎርፍ ከ 100 ሰዎች በላይ መሞታቸውን አስታወቀ

ኢሳት (ግንቦት 5 ፥ 2008)

ሰሞኑን በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በከፍተኛ ሁኔታ የዘነበውን ዝናብ ተከትሎ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ፣ ከ100 በላይ ዜጎች በመሬት መደርመስና መሞታቸውንና በደራሽ ጎርፍ መወሰዳቸውን መንግስት አስታወቀ።

በወቅታዊ ጎዳዮች ላይ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ የሰጡት የመንግስት ኮሚውኒኬሽን ሚኒስትር አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ከመጋቢት ወር ጀምሮ በተከሰተው በዚሁ ጎርፍ አያሌ ዜጎች ተጎድተዋል በማለት ተናግረዋል።  አቶ ጌታቸው ማክሰኞ ዕለት ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ከጎርፍ ጋር በተያያዘ የሟቾች ቁጥር 50 ያህል እንደነበር የገለጹ ቢሆንም፣ ከሁለት ቀን በኋላ ሃሙስ ዕለት የሟቾቹን ቁጥር ወደ ለምን 100 እንደደረሰ የገለጹት ነገር የለም።

የመንግስት ኮሚውኒኬሽን ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ ትናንት ሃሙስ ለመገናኛ ብዙሃንን መግለጫ ሲሰጡ እንደተናገሩት 32 ሰዎች የሞቱት በደቡብ ኢትዮጵያ ከጎርፍ ጋር ተያይዞ በተከሰተው የመሬት መንሸራተት እንደሆነ ገልጸው፣በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ብዛት ያላቸው ሰዎች በደራሽ በጎርፍ መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

በጎርፉ ምክንያት ከ100 በላይ የቀንድ ከብቶች እንደሞቱና በመቶ ሄክታሮች የሚገመት አዝመራ መውደሙን ለመገናኛ ብዙሃን ሃሙስ በሰጡት መግለጫ አክለው ተናግረዋል።

አቶ ጌታቸው መንግስት በጎርፍ በሚጠቁ አካባቢዎች ሰዎችን ወደሌላ አካባቢ በመውሰድ ማስፈር ጀምሯል ቢሉም፣ ሰፈራው በየትኛው አካባቢና መቼ እንደተደረገ ያሉት ነገር የለም።