ነሃሴ ፴ ( ሠላሳ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ኢትዮጵያ ውስጥ በተቃዋሚዎች ላይ እየተፈጸመ ያለው አደገኛ እርምጃ መንግስታቸውን በከፍተኛ ደረጃ ማሣሰቡንና በጉዳዩ ዙሪያ ምርመራ እንዲደረግ መጠየቃቸውን በተመድ የአሜሪካ ቋሚ መልዕክተኛና የፕሬዚዳንት ኦባማ ካቢኔ አባል የሆኑት አምባሳደር ሳማንታ ፓወር በጁባበሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።
አምባሳደር ሳማንታ ፓወር ትናንት ከቀትር በኋላ በሰጡት በዚሁ መግለጫቸው የመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት ልኡካን በደቡብ ሱዳን ያደረጉትን ጉብኝት ማጠናቀቃቸውን በመጥቀስ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ ከአፍሪካ ህብረት ባለሥልጣናት ጋር ለመወያዬት ዛሬ ሰኞ ወደ አዲስ አበባ እንደሚያቀኑ ገልጸዋል።
ሳማምታ ፓወር በኢትዮጵያ የተከሰተውን ግጭት “እጅግ አደገኛ” ሲሉ መጥራታቸውን የአኦሶሺየትድ ፕሬስ ዘገባ ያመለክታል። በመሆኑም ግልጽና ገለልተኛ ምርመራ እንዲደረግ ጥሪ አቅርበዋል።
ከዚህም ባሻገር ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞውን ይገልጽ ዘንድ እንዲፈቅድ የዩናይትድስቴትስ መንግስት- የኢትዮጵያ መንግስትን መጠየቁን ሳምንታ ፓወር ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ላለፉት ወራት በስፋት የተዛመተውን የነጻነት ጥያቄ ያነገበ ተቃውሞ ተከትሎ መንግስት በግድያ፣ በድብደባና ኢንተርኔት በመዝጋት ክስ እየተመሰረተበት ይገኛል።
የአፍሪካ ህብረት ራሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ያለው አለመረጋጋት እያሣሰበው እንደመጣ መግለጫ ማውጣቱን አሶሺየትድ ፕሬስ አውስቷል።
በኢትዮጵያ የአሜሪካ ተሰናባች አምባሳደር ፓትሪሽያ ሀስላክ ኢትዮጵያ ውስጥ ሰዎች ያለህግ እንደሚታሰሩና የኤምባሲው ሠራተኞች ጭምር ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ነገር እንደሚፈሩ የተናገሩት ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ነበር።