የኢትዮጵያ መንግስት በቡና ነጋዴዎች ላይ እስከ 5 አመት ድረስ የሚያስቀጣ አዲስ መመሪያ ተግባራዊ አደረገ

ኢሳት (ሚያዚያ 28 ፥ 2008)

የኢትዮጵያ መንግስት ከቡና ንግድ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ገቢ ለማሳደግና በቡና ነጋዴዎች ላይ እስከ 5 አመት እስራትን የሚያስቀጣ አዲስ የቁጥጥር መመሪያን ተግባራዊ አደረገ።

በሃገሪቱ በቡና ንግድ ላይ ተስማርተው የሚገኙ አካላት ደረጃቸውን ካልጠበቁና ካልተሰባበሩ ቡናዎች በስተቀር ሁሉንም ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ ማቅረብ እንዳለባቸው መመሪያው ማስገዱዱን ዘ-ዎል ስትሪት የተሰኘ ጋዜጣ ዘጓል።

አዲሱን መመሪያ ተግባራዊ በማያደርጉ ቡና ነጋዴዎች ላይም ከ40ሺ ብር በላይ የገንዘብ ቅጣትና እስከ አምስት አመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ሊተላለፍ እንደሚችል የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ልማት ባለስልጣን በመመሪያው ደንግጓል።

ይሁንና፣ በቡና ንግድ ላይ ተስማርተው የሚገኙ አካላት የአለም የቡና ዋጋ በመቀነሱ ምክንያት ምርታቸውንለሃገር ውስጥ ገበያ ቢያቀርቡ የተሻለ ዋጋን ሊያገኙ እንደሚችሉ በመግለጽ በመመሪያው ላይ ያላቸውን ቅሬታ ገልጸዋል።

የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ከቡና ንግድ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ለማሳደግ ሲባል አዲሱ የቁጥጥር መመሪያ ተግባራዊ መደረጉን  ለጋዜጣው በሰጡት ምላሽ አስረድተዋል።

በተያዘው የፈረንጆች አመት ሃገሪቱ ከቡና ንግድ ወደ 800 ሚሊዮን ዶላር ገቢን ለማግኘው እቅድ የያዘች ሲሆን፣ እቅዱም ከባለፈው አመት ጋር ሲነጻጸር የ13 በመቶ ብልጫ እንዳለው ታውቋል።

በአለም የቡና ምርት ላይ የታየው የአስር በመቶ የዋጋ ቅናሽ ኢትዮጵያን ጨምሮ በብራዚልና በሌሎች የቡና አቅራቢ ሃገራት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሮ የሚገኝ እንደሆነም ዘዎል ስትሪት ጆርናል ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።

የዓለም ዋነኛ የቡና ላኪ ሃገር የሆነችው ብራዚል የመገበያያ ገንዘብ ከዶላር ጋር ያለው የመግዛት አቅም በቅርቡ በ30 በመቶ መቀነሱ የለም የቡና ዋጋ እንዲቀንስ ማድረጉንም ለመረዳት ተችሏል።

ይህም የዋጋ መቀነስ በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖን ያሳደረ ሲሆን መንግስት ከፍተኛ መጠን ያለው ቡና በመላክ ገቢውን ለማካካስ ጥረትን እያደረገ እንደሆነም የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች አስረድተዋል።

በሃገሪቱ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ በዚሁ የግብርና ምርት ላይ የራሱን አሉታዊ ጎን እንደሚያሳድርም ባለሙያዎች ይገልጻሉ።