(ኢሳት ዲሲ–መስከረም 15/2011)የኢትዮጵያ መንግስት በገባው ቃል መሰረት ሰብዓዊ መብትን እንዲያከብር አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪ አቀረበ።
የሃገሪቱን ወህኒ ቤቶች ከሕግ አግባብ ውጭ ከታሰሩ ሰዎች ነጻ በማድረግ የጀመረውን ርምጃ መቀልበስ አይኖርበትም ሲልም አሳስቧል።
ከሰሞኑ ግጭት ጋር በተያያዘ ሰልፍ በመውጣታቸው የታሰሩ በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪ አቅርቧል።
“የጅምላ አፈሳና እና እስራት በሰብዓዊ መብት አከባበር የታየውን ርምጃ ስጋት ውስጥ ጥሎታል” በሚል ርዕስ ዓለም ዓቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምነስቲ ኢንተርናሽናል መግለጫ አውጥቷል።
ፖሊስ ከሶስት ሺህ ሰዎች በላይ መታሰራቸውን በተመለከተ የሰጠውን መግለጫ በአስረጅነት በመጥቀስ መንግስት ከህግ ውጭ ሰዎች ማሰሩን ያቁም ሲል ጥሪ አቅርቧል።
ባለፉት ወራት የሃገሪቱን ወህኒ ቤቶች ያለፍርድ ለታሰሩ ሰዎች ነጻ ለማድረግ የጀመረውን የሚደነቅ ሙከራ ሌሎችን ከህግ ውጭ በማሰር ሊደግመው አይገባም ሲልም አሳስቧል።
በሃገሪቱ ከተከሰተው ግጭት ጋር በተያያዘ ሰልፍ በመውጣታቸው የታሰሩት በሙሉ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ ጥሪ ያቀረበው አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሺሻ በማጨስና ከጫት ጋር በተያያዘ የታሰሩትን በተመለከተም ተቃውሞውን አቅርቧል።
ይህ በዓለም አቀፍ ህግ ያልተከለከለ ድርጊት እንደሆነም በማስታወስ በወንጀል የሚያስጠይቅ ከሆነም እንዲከሰሱ ያለዚያም እንዲለቀቁም ነው ያሳሰበው።
የታሰሩት በሙሉ ስቃይ እንዳይደርስባቸው ከጠበቃም ሆነ ከቤተሰባቸው ጋር እንደገናኙ ይፈቀድላቸው ዘንድም አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪውን አቅርቧል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮምሽነር ሜጀር ጀነራል ደግፌ በዲ ትናንት በሰጠው መግለጫ አዲስ አበባ ውስጥ 3ሺህ ያህል መታሰራቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
ከነዚህ ውስጥ ብዙዎቹ ወዲያው መለቀቃቸውን 1ሺህ 200 የሚሆኑት ደግሞ ለታህድሶ ጦላይ መወሰዳቸውን ገልጸዋል። ትምህርታቸውን ሲጨርሱም ይለቀቃሉ ብለዋል።
ሆኖም 174 ሰዎች ክስ እንደሚመሰረትባቸው መግለጻቸው ይታወሳል። ከመስከረም 2-7/2011 28 ሰዎች አዲስ አበባ ውስጥ መገደላቸውንም ገልጸዋል። ከነዚህ ውስጥ 7ቱ በፖሊስ የተገደሉ ናቸው ።