ኢሳት (ሃምሌ 4 ፥ 2008)
ሰኞ በመላዉ ኢትዮጵያ መሰጠት የጀመረዉን የ12ኛ ክፍል ማጠናቀቂያ ብሔራዊ ፈተና ምክንያት በማደረግ መንግስት የማህበራዊ ድረ-ገፆችን ዘጋ።
ከቀናት በፊት ብሔራዊ ፈተናዉ ለሁለተኛ ጊዜ አፈትልኮ ስለመዉጣቱ ሲገለፅ ቢቆይም የትምህርት ሚኒስትር የተሰራጨዉን መረጃ በማስተባበል የማህበራዊ ድረ-ገፅችን በመዝጋት የተወሰደዉ እርምጃ ተፈታኞች ፈተናዉን ተረጋግተዉ እንዲወስዱ ነዉ ሲል ገልጿል።
በአብዛኛዉ ህዝብ ዘንድ የሚታወቁት የፌስቡክ ፣ ትዊተር ፣ ቫይብር እና ሌሎች አገልግሎቶች ከጥቂት ቀናት በፊት አገልግሎት እንዳይሰጡ መደረጉን BBCን ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።
የመንግስት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸዉ ረዳ እርምጃዉ ጊዜያዊ መሆኑን ከBBC ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስታዉቀዋል። ይሁንና የማህበራዊ ድረ-ገፅ ተጠቃሚዎች መንግስት በይፋ የብሔራዊ ፈተናዉን በማመካኘት አገልግሎቱ ለተወሰነ ጊዜ ስለመቋረጡ ቢገልፅም ችግሩ የቆየ መሆኑን በመግለፅ ላይ ናቸዉ።
ስማቸዉን መግለፅ ያልፈለጉ ነዋሪዋችና ጋዜጠኞች በበኩላቸዉ ድርጊቱ ገና ጅማሪ መሆኑንና በመቀጠል አገልግሎቱን ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጠርና ለማስቀረት እርምጃዎች ሊወሰዱ እንደሚችሉ ያላቸዉን ስጋት ለBBC ገልፀዋል።
ባለፈዉ ወር የሀገሪቱ ፓርላማ በኢንተርኔት አጠቃቀም ዙሪያ ያሉ አገልግሎቶችን ለመቆጣጠር ያስችላል የተባለ ህግ ማፅደቁ የሚታወስ ሲሆን በዚሁ ህግ መሰረት አመጽን ያነሳሳሉ የተባሉ ፁሁፎችንና ምስሎችን ያሰራጨ ተጠቃሚ እስከ አምስት ዓመት የሚደርስ እስራት እንደሚጣልበት ተደንግጓል።
ከቀናት በፊት የተወሰደዉ እርምጃ እቅዱን ለመፈተሽና የህዝቡን ምላሽ ለማየት ሊሆን እንደሚችል ለደህንነታቸዉ ሲሉ ስማቸዉን መግለፅ ያልፈለጉ ነዋሪዎች ለBBC አስረድተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዪ ከተሞች የሚኖሩ ነዋሪዋች በማህበራዊ ድረ-ገፅች ላይ የተወሰደዉን እርምጃ ተከትሎ መደበኛ የኢንተርኔት አገልግሎት ማግኘት እንዳልቻሉ በመግለፅ ላይ መሆናቸውን ታዉቋል።
መንግስት እርምጃዉ በተወሰኑ የኣገልግሎቱ አይነቶች ላይ መሆኑን ቢገልፅም የኢንተርኔት ተጠቃሚዋች ምንም አይነት ኣገልግሎቱ ማግኘት እንዳልቻሉ ለሀገር ዉስጥ መገናኛ ብዙሀን ገልፀዋል።