(ሚያዚያ 24 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ መንግስትና የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች ከተጠለፉት ህጻናት መካከል 32ቱ ህጻናት ስለመገኘታቸው ጉዳይ አለመዘገባቸው ትዝብት ፈጠረ።
ከሁለት ሳምንት በፊት በጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን በመጡ በሙርሌና ዲንቃ ጎሳ ታጣቂዎች በግፍ ታፍነው ከተወሰዱት 125 ኢትዮጵያውያን ህጻናት፣ 32ቱ መገኘታቸውን የደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት መግለጻቸውን “ዘስታር” ቅዳሜ ዕለት መዘገቡ ይታወሳል።
ከጋምቤላ ክልል ጋር በሚዋሰነው የደቡብ ሱዳን የቦማ ግዛት አስተዳዳሪ የሆኑት ሚስተር ኦጋቶ ቻን፣ የግዛቱ የበታች ሹማምንቶች፣ ታፍነው ከተወሰዱት ህጻናት 32ቱን ሊኳንጎሌ አስተዳደር ስር ከሚገኙ ሶስት ቀበሌዎች ሰብስበው መልሰዋቸዋል ሲል አሶሽየትድ ፕሬስን ዋቢ በማድረግ ዘስታር የተባለው የድረገጽ ጋዜጣ አስነብቧል። የሙርሌ ታጣቂዎች ወላጆቻቸውን በመግደል የተወሰኑ ህጻናንትን በዚሁ ክልል ለከብት ጥበቃ እንዲሰማሩ እንዳስቀመጧቸውም ታውቋል።
የቦማ ግዛት አስተዳዳሪ የሆኑት ሚስተር ቻን ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት፣ ከሶስቱ መንደሮች የተሰበሰቡት ኢትዮጵያውያን ህጻናት ወደክልሉ ርዕሰ ከተማ ፒቦር ከተወሰዱ በኋላ እንደገና ወደጁባ ተልከው ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በድርድር መልክ ተላልፈው ይሰጣሉ ብለዋል።
የቦማ ግዛት የበታች የመንግስት አስተዳደር አካላት በግፍ ተጠልፈው የተወሰዱትን ሌሎች ህጻናትን በክልሉ እየፈለጉ እንደሆነ አስተዳዳሪው ሚስተር ቻን ለአሶሽዬትድ ፕሬስ ገልጸዋል። ሆኖም የደቡብ ሱዳን የክልል ባለስልጣናት 32ቱ ህጻናት ሰለመገኘታቸው ቢገልጹም፣ ህጻናቱን አፍኖ ወስዷል ስለተባለው የሙርሌ ታጣቂ ሃይል ግን የሰጡት ዝርዝር መረጃ የለም።
የኢትዮጵያ መንግስት የሙርሌ ጎሳ አባላት የሆኑና ጥቃቱን ፈጽመዋል በተባሉ ታጣቂዎች ላይ እርምጃን ለመውሰድ ህጻናቱ የታገቱበት አካባቢ ከብቤያለሁ በአጭር ጊዜ አስለቅቃቸዋለሁ ሲል ቢቆይም ይህ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ደቡብ ሱዳን ድረስ ዘልቆ መግባቱና ከበባ መፈጸሙን የሚያመላክት መረጃ አልተገኘም።
ባለፈው ሳምንት ሶስት በደቡብ ሱዳን ቦማ ግዛት የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ቡድኖች በጋራ ባወጡት መግለጫ የኢትዩጵያ መንግስት ከሱዳን ብሄራዊ መንግስትና ከቦማ ግዛት አስተዳደር ጋር የሰላም ንግግር በማድረግ የተጠለፉትን ህጻናት “በሰላም” ማስመለስ ይኖርበታል ማለታቸውንና፣ በጥቃቱ ለተጎዱ ቤተሰቦች የደቡብ ሱዳን መንግስት ካሳ እንዲከፈል ጥሪ ማቅረባቸውን ይታወሳል።
ከሁለት ሳምንት በፊት በጋምቤላ ክልል በሚኖሩ የኑዌር ጎሳ አባላት ላይ በሙርሌና ዲንቃ ጎሳ ታጣቂዎች ተፈጽሟል በተባለ በዚሁ ጥቃት ከ208 በላይ ኢትዮጵያውያን መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከ108 የሚበልጡ ህጻናትና ሴቶች ታግተው መወሰዳቸው በአለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ርዕስ ሆኖ የአለም መገናኛ ብዙሃንን ሲያነጋግር ቆይቷል።
ህጻናቱ ጁባ መግባታቸው የትገለጸው ባለፈው ቅዳሜ ቢሆንም፣ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ሰኞ ድረብ በኢትዮጵያ መንግስት በኩል የተሰጠ መግለጫ የለም ፥ የመንግስት መገናኛ ብዙሃንም በጉዳዩ ላይ ያሉት ነገር የለም።