ኢሳት (ህዳር 13 ፥ 2009)
ላለፉት ስምንት አመታት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገሉት አቶ ኢሳያስ ባህሬ ከሃላፊነታቸው ተነሱ።
የባንኩ ሃላፊ ከስልጣናቸው እንዲነሱ የተደረገበት ምክንያት ያልታወቀ ሲሆን፣ ከስራ ስለመሰናበታቸው የሚገልጽ የጽሁፍ ደብዳቤ ከፋይናንስ መቆጣጠሪያ ኤጀንሲ ሃላፊ አቶ ስንታየሁ ወልደሚካዔል ተፈርሞ የደረሳቸው መሆኑን በሃገር ቤት ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ከተያዘው ሳምንት ጀምሮ ለስምንት አመታት ያህል ጊዜ ካገለገሉበት የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የተነሱት አቶ ኢሳያስ በብሄራዊ ንግድ ባንክ ሲያገለግሉ እንደነበርም ታውቋል።
በሃላፊው ምትክ እስካሁን ድረስ የተሰየመ ሰው አለመኖሩን የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የህዝብ ግንኙነት ክፍል ለመገናኛ ብዙሃን ገልጿል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በሃገሪቱ ሊገነቡ ከታሰቡ ከአራት የስኳር ፕሮጄክቶች ጋር በተገናኘ ከ77 ቢሊዮን ብር በላይ ኪሳራ ደርሶበት እንደነበር ከወራት በፊት ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
ባንኩ ከስኳር ፕሮጄክቶች ጋር በተያየዘ ከደረሰበት ኪሳራ በተጨማሪ በጋምቤላ ክልል የእርሻ መሬትን ለውጭ በለሃብቶች በሊዝ ለመስጠት በተከናወነ ሂደት በቢሊዮን የሚቆጠር ኪሳራም እንደደረሰበት ለመረዳት ተችሏል።
በጋምቤላ ክልል በአንድ ይዞታ ላይ የኢንቨስትመንት ፈቃድን የወሰዱ በርካታ ባለሃብቶች ተመሳሳይ መሬትን በመረጃነት በማቅረብ ከባንኩ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ በብድር ሲወስዱ መቆየታቸውን የልማት ባንኩ ጊገልጽ ቆይቷል።
ቁጥራቸው ያልተገለጸ የውጭና የሃገር ውስት ባለሃብቶች በዚሁ ድርጊት የተቀበሉትን ብድር ይዘው ከሃገር የተሰወሩ ሲሆን፣ መንግስት ከተወሰኑ የህንድ ኩባንያዎች ገንዘብ ለማስመለስ ጥረት እያደረገ መሆኑ ታውቋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በክልሎች ከኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ የደረሰበትን ከፍተኛ ኪሳራ ተከታትሎ መንግስት የእርሻ ቦታን ለባለሃብቶች መስጠት ማቆሙ ይታወሳል።
ባንኩ ደርሶበታል የተባለን በቢሊዮን የሚቆጠር ብር ኪሳራ ለማጣራት ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ተጠሪ የሆነ አካል ተቋቁሞ ምርመራን ሲያካሄድ መቆየቱን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አካላት አስረድተዋል።
ይሁንና የምርመራ ቡድኑ የደረሰበትን የምርመራ ውጤት በተመለከተ የተሰጠ ይፋዊ መረጃ ባይኖርም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከስኳር ፋብሪካዎች ግንባታና ከመሬት አሰጣጥ ጋር በተገናኘ በመቶ ቢሊዮኖች ብር የሚቆጠር ኪሳራ እንደደረሰበት የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የባንኩ ፕሬዚደንት ከሃላፊነት መነሳት ከዚሁ ኪሳራ ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው የተወቀ ነገር የለም።
አቶ አባይ ጸሃዬ የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ሃላፊ ሆነው ባገለገሉ ጊዜ ባንኩ ከፕሮጄክት ርክክብ እና እቃዎች ግዢ ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ኪሳራ ደርሶበት እንደነበር ምንጮች ለኢሳት ማሳወቃቸውን መዘገባችን የሚታወስ ነው።