ኢሳት (መጋቢት 22 ፥ 2009)
በ5 ቢሊዮን ብር ብክነት የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ልማት ባንክና አዲሱ አስተዳደር በጋምቤላ ከሚገኙ ኢንቨስተሮች ጋር የጀመሩት ውዝግብ ቀጥሏል። የቀድሞ የባንኩ ፕሬዚደንት አቶ ኢሳያስ ባህረን የተኩት አቶ ጌታሁን ናና በጋምቤላ እርሻ ኢንቨስትመንት ላይ በተሰማሩ የትግራይ ተወላጆች ወቀሳ የቀረበባቸው ሲሆን፣ የኢሳትን ወሬ እየሰማችሁ ተሽመድምዳችኋል በማለት ለደርግና ለግንቦት 7 ኮሎኔሎች ማበደር ፈልጋችሁ ነው ወይ ሲሉ ጠየቁ።
ባለፈው ቅዳሜ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ አዲስ አበባ ከተማ በተጠራው ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት፣ አዲሱን ፖሊሲ የተቃወሙ የማህበራት መሪዎችና ተወካዮች በጠ/ሚ/ሩ የተቋቋመውን በቀድሞው የውሃና ኤነርጂ ሚ/ር በአቶ አለማየሁ ተገኑ የተመራውን ኮሚቴ ጥናት ያብጠለጠሉ ሲሆን፣ ጥናቱ ለጠላቶቻችን በድብቅ ተላልፎ ተሰጥቷል ሲሉም መክሰሳቸውን አዲስ አበባ የሚታትተመው ሰንደቅ ጋዜጣ በዝርዝር ዘግቧል።