ኢሳት (ሚያዚያ 24 ፥ 2009)
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ካሉት አምስት ምክትል ፕሬዚደንቶች አራቱን ማክሰኞ ሚያዚያ 24 ፥ 2009 ጀምሮ ከሃላፊነት አነሳ።
አቶ ታደሰ ሃቲያ የክሬዲት (ብድር) ማኔጅመንት ምክትል ፕሬዚደንት፣ አቶ ተካ ይብራህ፣ የኮርፖሬት አገልግሎት፣ አልማዝ ጥላሁን የፋይናንስና ባንኪንግ ማኔጅመንት እንዲሁም አቶ ደረጀ አውግቸው የድጋፍ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚደንቱ ከሃላፊነታቸው የተነሱ ባለስልጣናት መሆናቸውን አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ዘግቧል።
ከስልጣናቸው በተነሱ ምክትል ፕሬዚደንቶች ምክትል አዳዲስ ሃላፊዎች የተተኩ ሲሆን፣ የልማት ባንክ ሃላፊዎች በምን ምክንያት እንደተነሱ በይፋ የሰጠው ምላሽ የለም።
ከምክትል ፕሬዚደንትነታቸው የተነሱት አራቱ ሃላፊዎች የወደፊት እጣ ፈንታቸውም ያልታወቁ ሲሆን፣ ባንኩ በጋምቤላ ክልል ሲሰጥ ከቆየው ሰፋፊ የእርሻ ልማት ጋር ከተያያዘ ለ 5 ቢሊዮን ብር ብክነት መጋለጡ ይታወቃል።
ከሁለት ወር በፊት ባንኩ ለረጅም አመታት በፕሬዚደንትነት ያገለገሉትን አቶ ኢሳያስ ባህረን ከስልጣን ማንሳቱ አይዘነጋም። ይሁንና የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ዋናው ፕሬዚደንቱም ሆነ አራቱ ምክትል ፕሬዚደንቶች ከጋምቤላው እርሻ ኢንቨስትመንት ብድር አሰጣቱ ጋር በተያያዘ ተጠያቂ ይሁኑ አይሁኑ የሰጠው መረጃ የለም።
የጋምቤላ ክልል መንግስስት በክልሉ ተደራራቢ ብድር በአንድ ይዞታ ላይ እንዲሰጥ አስተዋጽዖ አድርገዋል ያላቸውን ከ20 የሚበልጡ ሰራተኞችንና ሃላፊዎችን ከስራ ማንሳቱ የሚታወስ ነው።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በክልሉ የደረሰበትን ኪሳራ ተከትሎ ለዘረፋ ሲሰጥ የቆየውን ብድርና ከአንድ አመት በላይ አቋርጦ ቆይቷል። ይሁንና የፌዴራል መንግስት መሬቱን የመስጠት ሂደቱ በክልሉ ብቻ እንዲያስተናግድ ወስኖ ብድር መስጠቱን ከወራት በፊት በአዲስ መልክ መጀመሩ ይታወቃል።
የብሄራዊ ባንክ በበኩሉ በንግድ ባንክ በኩል ሲሰጥ የነበረው የልማት ፕሮጄክቶች ብድር ቀርቶ ልማት ባንክ ብድሩን እንዲያቀርብ ከሳምንት በፊት አዲስ መመሪያን አውጥቷል።
ይሁንና በርካታ ባለሃብቶች የብሄራዊ ባንክ የወሰደው ዕርምጃ በብድር አቅርቦቱ ላይ እንግልት ያስከትላል በሚል ቅሬታን እያቀረቡ ይገኛል።