ሰኔ ፱ ( ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፱ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በቅርቡ በባህርዳር ከተማ የአማራ ክልል ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ከባለሃብቶች እና አበዳሪ አካላት ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ ፣ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኪሚሽነር አቶ መላኩ አለበል፣ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በአማራ ባለሃብቶች ላይ በደል እየፈጸመው ነው ብለዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ደረጃ ንግድ ኢንዱስትሪና ገበያ ልማት ቢሮ ሃላፊ አቶ ተስፋየ ጌታቸውም፣ በክልሉ ውስጥ ያሉ ባለሃብቶች ከልማት ባንክ ብድር ሲጠይቁ ከሚፈቀድላቸው ይልቅ የሚከለከሉበት እጅግ ከፍተኛ ነው ይላሉ። የልማት ባንኩን በመወከል በስብሰባው ላይ የተገኙት አቶ ጌታሁን፣ የክልሉን ባለሀብቶች ብድር የምከለክለው፣ የህዝብ ሃብት ለመጠበቅ ሲባል ነው በማለት የሰጡት መልስ ፣ አቶ መላኩ የባንኩን አሰራር ገሃድ እንዲያወጡት አስገድዷቸዋል።
“ልማት ባንክ እኮ ማንም እየገባ እየዘገነው የሚሄድ ተቋም ነው” ያሉት ተስፋየ፣ ‘የህዝቡን ሃብት ለመጠበቅ ስንል ነው ብድር የማንሰጠው’ ተብሎ የቀረበልን ምክንያት፣ ለህዝቡ እንዲህ ብለን ልንነግረው እንችላለን፣ እኛ ግን እንዲህ ልንባል አንችልም፣ ሚስጢሩን ስለምናውቀው” ብለዋል። ባለሃብቶች ፐሮጀክት አቅርበው ብድር ሲጠይቁ፣ መቀሌ ላይ ተሞክሮ የከሸፈ ፕሮጀክት ነው ተብለው ከማእከል ደብዳቤ ተጽፎ ብድር ይከለከላሉ፣ የመቀሌው ባለሀብት ሌላ የኮምቦልቻ ባለሀብት ሌላ ሲሉ ባለስጣኑ ይገልጻሉ ።
“የትኛው ፕሮጀክት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ የማያዋጣው፣ ልማት ባንክ ለራሱ ዜጎች እየከለከለ ለውጭ ዜጎች አበድሮ አልተጭበረበረም?” ሲሉ የሚጠይቁት ባለስልጣኑ፣ የአዲስ አበባ ህንጻ በግል ባንኮች ሳይሆን በልማት ባንክ ገንዘብ እንደሚገነባ አጋልጠዋል። “በማንፋክቸሪንግ ስም ብድር ወስዶ ህንጻ እየተገነባበት ነው ፣ በጋምቤላና ቤንሻንጉል ያለው በእርሻ ስም የሚወሰደው ብድር ፣ ህንጻ የሚሰራበት ጎንደር ላይ ። ጎንደር ውስጥ ያሉ በለሃብቶች፣ ‘እኛ ህንጻውን ለመገንባት የወሰድነው ገንዘብ፣ ከልማት ባንክ ሳይሆን፣ ጋምቤላ እና ቤንሻንጉል ላይ እርሻ እናለማለን በማለት ከወሰዱ ባለሀብቶች ላይ ነው’ በማለት የትግራይ ባለሀብቶች በቤንሻንጉልና በጋምቤላ የእርሻ ስራ እንሰራለን በሚል ከፍተኛ ገንዘብ ከልማት ባንክ በመውሰድ ፣ ገንዘቡን አዲስ አበባ ውስጥ ህንጻዎችን እንደሰሩባቸው እንዲሁም የጎንደር ባለሀብቶች ከተበዳሪዎች ላይ ብድር ወስደው ህንጻዎችን እንደሰሩ ተናግረዋል። እነሱ ከልማት ባንክ ወስደው ለሌላው ያበድራሉ፣ እነሱ ህንጻ ይሰራሉ በማለት የትግራይ ባለሃብቶችና የልማት ባንክ ባለስልጣናት በጋራ የሚሰሩትን ስራ ገልጸዋል።
ልማት ባንክ ውስጥ ጉቦ ሳይሰጥ ገንዘብ መበደር እንደማይቻልም በእለቱ በቀረበው ጥናት ላይ ተጠቅሷል።
በሌላ በኩል በአዊ ዞን እንጅባራ ላይ ያሉ ባለሃብቶች “ ከብሎኬት ድርደራ ወደ እንዱስትሪ ግቡ እየተባለን እየተጠየቅን ነው፣ ለመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ እንዱስትሪ ግቡ የምትሉን፣ መብራት፣ ውሃና ብድር” አለን ሲሉ ጠይቀዋል። እንኳንስ ኢንዱስትሪ ሊያንቀሳቅስ የሚችል፣ ለመበየጃ የሚሆን እንኳ መብራት የለም የሚሉት ባለሀብቶች፣ በመንግስት የሚሰበከውና መሬት ላይ ያለው እውነታ የተለያየ ነው ብለዋል።