(ኢሳት ዜና–ነሐሴ 3/2009) የመንግስት የፋይናንስ ድርጅቶች ዳይሬክተር የኢትዮጵያ ልማት ባንክ በብድር የሰጠውን ገንዘብ በማስመለስ ረገድ ችግር እንደነበረበት አስታወቁ።
በአመቱ የተበላሸ ብድር መጠንም በከፍተኛ ደረጃ በማሻቀብ 25 በመቶ መድረሱ ተገለጿል።
ልማት ባንኩ ከጋምቤላ የእርሻ ኢንቨስትመነት ጋር በተያያዘ ከፍተኛ የሀገር ሀብት ማባከኑን በራሱ በመንግስት የተካሄደው ጥናት አረጋግጧል።
የመንግስት የፋይናንስ ድርጅቶች ዳይሬክተር ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ ልማት ባንኩ የአመቱን የተበላሸ ብድር መጠን ከነበረበት ወደ 9 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር ለማውረድ ቢያቅድም ይበልጥ ከፍ ብሎ ወደ በ25 በመቶ ማሻቀቡን ተናግረዋል።
በባለሙያዎቹ ዘንድ የተበላሸ ብድር የሚባለው ባንኩ ያበደረውን ገንዘብ መመለስ የማይችልበት ሁኔታ ሲፈጠር እንደሆነም ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከጋምቤላ እርሻ ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ ያበደረው 5 ቢሊየን ብር መባከኑ በራሱ በመንግስት በተዋቀረ የጥናት ቡድን መረጋገጡ ይታወሳል።
ከልማት ባንኩ ብድሩን የወሰዱትና በጋምቤላ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት የትግራይ ተወላጆች ለእርሻ የወሰዱትን ብድር በአዲስ አበባና በትግራይ ህንጻ እንደገነቡበት የተወሰኑትም ገንዘቡን ይዘው የደረሱበት አለመታወቁ ሲገለጽ ቆይቷል።
በ5 ቢሊየን ብር የሀገር ሀብት ብክነት ዋናው ሃላፊና ተጠያቂ የሆኑት የህወሃት አባሉ የልማት ባንኩ ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ ባህረ በህዳር 2009 ከስልጣን ቢነሱም ተጠያቂ አልሆኑም።
ከሙስና ጋር በተያያዘ በሚወሰዱ ርምጃዎች በግንባር ቀደምትነት ይጠየቃሉ ከሚባሉት አንዱ
እርሳቸው ቢሆኑም ሌቦቹን የማሰርና የማሳደዱ ዘመቻ ግን ልማት ባንኩን አልጨመረም።
የሕዝባዊ ወያኔ ሀርነት ትግራይ /ሕወሃት/ንብረት የሆነው ኢፈርት የዛሬ 20 አመት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያለማስያዢያ የተበደረው 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር የተበላሸ ብድር በሚል ወደ ልማት ባንክ መዛወሩንና ሕወሃት ከተጠያቂነት ነጻ መደረጉን የባንኩ ምንጮች ያስታውሳሉ።