ህዳር ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፭ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የኢትዮጵያ ህዝብ በሚደርስበት የኢኮኖሚና የፖለቲካ በደል የሚያሰማውን የተናጥል ቁጣ በጋራ ማሳየት ይገባዋል ሲሉ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ገልጡ።
የኢሀዲግ መንግስት ለፓርቲው እንጂ ለህዝብ ደንታ የለውምም ብለዋል።
የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በሀገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ባደረጉት ውይይት እንደገለጹት የኢትዮጵያ ህዝብ ብሶቱን ቋጥሮ በማጉረምረም ላይ የሚገኝ ነው ፤ ቁጣውም ቢኋን በተናጠል የሚገለጽ ነው፤ ይህ የተናጥል ቁጣና ማጉረምረም ግን እንደሌሎች ሀገሮች በጋራና በአንድነት ሊገለጽ ይችላል ብለዋል።
እስከ አሁን እንደታየው ማህበራዊ፣ ኢኮኖምሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮቹን ይዞ ሰቆቃና ብሶቱን በተናጥል ወይም በጥቂት ቡድን ደረጃ የማርራል እንጂ በጋራ ሆኖ ድምጹን አላሰማም ያሉት ዶ/ር ነጋሶ ይህ ንዴቱና ብሶቱ ወደ ህብረተሰባዊ ንዴትና ቁጣ አልተለወጠም ብለዋል።
በሌሎች ሀገሮች የዳቦና የነዳጅ ዋጋ ላይ ትንሽ ጭማሪ ከታየ የህብረተሰብ ንዴቶች ይገነፍላሉ በኛ ሀገር ግን ከተናጥል ቁጣና ንዴት አልፎ ወደተደራጀና ህዝባዊ የእንቢተኝነት እንቅስቃሴ አልተለወጠም ያሉት የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አንባገነንነትና ለህዝብ ብሶት ግድ የሌለውን መንግስት ለመፈተን የተደራጀና ህብረተሰባዊ ቁጣ ያስፈልጋል ብለዋል።
ህዝባዊ ጥያቄንና ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ለማፈን ሲል ገዥው ፓርቲ ህገመንግስት ይጥሳል ፤ ህግ በማውጣት ህግ አስከብራለሁ ብሎ ሰባዊ መብቶችን ይጥሳል ብለዋል።