ኢሳት (ጥቅምት 23 ፥ 2009)
በአራት ድርጅቶች በቅርቡ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ አመራሮች የፊታችን አርብ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ አስታወቁ።
የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ አመራሮች ጋዜጣዊ መግለጫውን ለመስጠት የፈለጉት ህብረታቸው ወደፊት ለመስራት ያቀዳቸውን ጉዳዮች ለማብራራት መሆኑን አስታውቀዋል።
በዋሽንግተን ዲሲ ፕሬስ ክለብ ከእኩለ-ቀን ጀምሮ በሚሰጠው የንቅናቄው አመራሮች ጋዜጣዊ መግለጫ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር መሪዎች አቶ ሌንጮ ለታና ዶ/ር ዲማ ነገዎ፣ የአፋር ህዝባዊ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ኮንቴ ሙሳ፣ የአርበኞች ግንቦት 7 አመራት አባል አቶ ሙሉነህ ኢዩዔል እንድሁም የሲዳማ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ሰብሳቢ አቶ በቀለ ዋዮ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል።
በኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ ምስረታ ለአማራው ህዝብ ድምጽ ለመሆን በግሉ በታዛቢነት የተገኘው አቶ ሃይለገብርዔል አያሌው በጋዜጣዊ መገልጫው እንደሚገኝም ተገልጿል።
ህወሃት/ኢህአዴግ በደረሰባት የሰብዓዊ መብት ረገጣ ለእስር ተዳርጋ የቆየችው ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ በጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደምትገኝም ከኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ ሁሉንም አሳታፊ ለማድረግ ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ድርጅቶች ጋር በመተባበር የህወሃት/ኢህአዴግ አምባገነን መንግስት ለመጣል እንደሚሰራ መገልጹ ይታወሳል።