(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 6/2010)
የአውሮፓ ፓርላማ በጠራውና ኢትዮጵያን በተመለከተው አስቸኳይ ስብሰባ ላይ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ የሽግግር ሰነድ ማቅረቡ ተገለጸ።
የሽግግር ሰነዱ አሁን በስልጣን ላይ ያለው የህወሃት አገዛዝ ከወደቀ በኋላ በኢትዮጵያ የሚደረገውን የሽግግር ስርዓት የሚያሳይ መሆኑ ተመልክቷል።
በስብሰባው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ ከፍተኛ አመራሮች ለኢሳት እንደገለጹት የአውሮፓ ፓርላማ የኢትዮጵያ ቀውስ አሳሳቢ መሆኑን በመረዳት ከዚህ ቀደም ይከተለው የነበረውን አካሄድ በመተው የለውጥ ሃይሎች የመፍትሄ ሀሳብ እንዲያቀርቡ ጠይቋል።
የአውሮፓ ፓርላማ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ የምክክር መድረክ ሲያዘጋጅ የዛሬው የመጀመሪያው አይደለም።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትኩሳት በተፈጠረ ቁጥር በተለይም ከተቃዋሚ ሃይሎች ጋር ስብሰባ መቀመጥ የተለመደ ነበር።
የዛሬው በአውሮፓ ፓርላማ የተዘጋጀው ስብሰባ ግን የተለየ ነው ይላሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ አመራሮች።
ከዚህ ቀደም የቀውሱ ፈጣሪ የሆነውን የህወሀት አገዛዝ በስልጣን ላይ እንዲቆይ የሚፈልጉት የምዕራብ መንግስታት መፍትሄውንም ከዚያው ከስርዓቱ የሚጠበቅ እንዲሆን ሲያደርጉ ቆይተዋል።
አሁን ኢትዮጵያ የደረሰችበት የቀውስ ደረጃ የበፊቱን አካሄዳቸውን እንዲቀይሩ እንዳደረጋቸው በስብሰባው ላይ የተጋበዙት አካላት ለኢሳት ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ዲማ ነገዎ እንደሚሉት የአውሮፓ ፓርላማ የኢትዮጵያ ቀውስ ያሳሰባቸው በመሆኑ ቀውሱን ለመፍታት የቀድሞውን አካሄድ ለመተው መፈለጋቸውን ፍንጭ ያሳዩበት ስብሰባ ነው የዛሬው።
ዶክተር ዲማ ኢትዮጵያ ውስጥ እየተከሰተ ያለው ቀውስ ለናንተም ይተርፋልና አስቡበት የሚል ግልጽ መልዕክት ዛሬ ለአውሮፓዎቹ እንዲደርሳቸው አድርገናል ሲሉ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ አሁን የምትገኝበት አሳሳቢ ቀውስ በስልጣን ላይ ባለው የህወሃት አገዛዝ መፍትሄ የሚገኝ እንዳልሆነ የተረዳው የአውሮፓ ፓርላማ ስርዓቱን ለመለወጥ የሚታገሉ ሃይሎችን በመጋበዝ ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ በተነጋገረበት በዛሬው መድረክ የተገኙት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ ተባባሪ ሊቀመንበር እንዲሁም የአርበኞች ግንቦት ሰባት ንቅናቄ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የአውሮፓ ፓርላማ በሁለት ምክንያቶች የዛሬው ስብሰባ እንደጠሩት ገልጸዋል።
አንደኛው የኢትዮጵያ ህዝብ በጋራ ትግል እያደረገ መሆኑን፣ የስርዓት ለውጥ ከመጣም ለኢትዮጵያ አደገኛ እንደማይሆን ለመፈተሽ ሲሆን ሁለተኛው በተቃዋሚዎች በኩል ከስርዓት ለውጥ በኋላ ያላቸውን ዝግጅት ለማወቅ የተዘጋጀ ስብሰባ መሆኑን ፕ/ር ብርሃኑ ጠቅሰው በአውሮፓ ፓርላማ በተጠየቅነው መሰረት የሽግግር ሰነድ አቅርበናል ብለዋል።
በስብሰባው ላይ የአውሮፓ ፓርላማም ሆነ ሌሎች የምዕራቡ መንግስታት ቢፈልጉም ባይፈልጉም የኢትዮጵያ ህዝብ የጀመረው ትግል ወደኋላ የማይቀለበስ መሆኑን በግልጽ እንዲያውቁት መደረጉን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ አመራሮች ገልጸዋል።
የአውሮፓ ፓርላማም እስከዛሬ በነበረው መንገድ መቀጠል ቀውሱን የሚያባብስ መሆኑን በመረዳት ከሌሎች አካላት ጋር እንደሚመካከርበት መግለጹን ለማወቅ ተችሏል።
በስበሳባው ላይ የተካፈሉት የአውሮፓ ፓርላማ አባል ማዳም አና ጎሜዝ የአውሮፓ ህብረት በውጭ የሚገኙና ለፍትህና ነጻነት የሚሰሩ ሚዲያዎችን በገንዘብ ማገዝ ይኖርበታል ማለታቸው ተጠቅሷል።
በስብሰባው ላይ ከተለያዩ የኢትዮጵያ የተቃዋሚ ሃይሎች የተወከሉ እንዲሁም በሰብዓዊ መብት ላይ ከሚንቀሳቀሱ የኢትዮጵያ ድርጅቶች የተጋበዙ ተወያዮች ተገኝተውበታል።