የኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅ ኦሮሞ ሃላፊነት አለበት ሲሉ ዶ/ር አብይ አህመድ ተናገሩ
( ኢሳት ዜና መስከረም 09 ቀን 2011 ዓ/ም ) ጠ/ሚኒስትር አብይ ይህን የተናገሩት በሊቀመንበርነት የሚመሩትን የኦህዴድን 9ኛ ድርጅታዊ ጉበኤ ሲከፍቱ ባሰሙት ንግግር ነው። ኦሮሞ “ የዚህን አገር አንድነት የማስጠበቅ ሃላፊነት አለበት” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያን አንድነት ለማፍረስና ለውጡን ለመቀልበስ የሚሞክሩ ሃይሎችንም አስጠንቅቀዋል። ከጠላቶቻችን ጋር ሆናችሁ የኦሮሞን ትግል ወደ ሁዋላ ለመመለስ የማታስቡን ከጠላቶቻችን ለይተን አናያችሁም ያሉት ዶ/ር አብይ፣ በኦሮሞ ስም መነገድ ማብቃት አለበት ብለዋል። አብሮ መቆም ማለት ጠዋት እዚህ ከሰዓት እዛ እየሄዱ መስራት አለመሆኑን ፣ በኦሮሞ ስም እየነገዱ ለውጡን ለመቀልበስ ለሚሞክሩ ሃይሎች ማስጠንቀቂያ ልከዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የአብዴንን ምልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጽ/.ቤት ሃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን፣ የኦሮሞና የአማራ ህዝብ ለዘመናት በታሪክ የተሳሰረ፣ ደስታና ችግሮችን አብሮ ያሳለፈ ህዝብ መሆኑን ገልጸዋል። ባለፉት 27 አመታት አማራና አሮሞን ለመለያየት ስራዎች ሲሰሩ እንደነበር የገለጹት አቶ ንጉሱ፣ አሁንም ይህንን አንድነት ሊሸረሽሩ የሚችሉ ሃይሎች የፍቅር ማርከሻ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል።
በጉባኤው ላይ የደኢህዴንና የህወሃት ተወካዮችም ንግግሮችን አድርገዋል።