ኢሳት (ኅዳር 15 ፥ 2009)
በቅርቡ በኢትዮጵያና በኬንያ ድንበር አካባቢ የተካሄደን ግጭት ተከትሎ የሁለቱ ሃገራት ተወካዮች በኬንያ ሞምባሳ ከተማ የጸጥታና ደህንነት ውይይት በማካሄድ ላይ መሆናቸው ተገለጸ።
ኢትዮጵያ የኦሮሞ ነጻነት ግንባት (ኦነግ) ታጣቂዎችን ለመያዝ በሚል በተደጋጋሚ የኬንያን ድንበር እየጣሰች መግባቷ በኢትዮጵያና ኬንያ መካከል ዲፕሎማሲያዊ አለመግባባት መፍጠሩን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ባለፈው ወር የኬንያ ድንበር ጥሰው የገቡ የኢትዮጵያ ወታደሮች ስድስት የኬንያ ፖሊሶችን አግተው የነበረ ሲሆን፣ ሃገሪቱ ድርጊቱን በመቃወም ወታደሮቿ በድንበር አካባቢ አሰማርታ መቆየቷን ዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ ዘግቧል።
ሁለቱ ሃገራት በድንበር ዙሪያ ያላቸው አለመግባባት እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ፣ ከ60 የሚበልጡ የኢትዮጵያና የኬንያ መንግስት ተወካዮች በጉዳዩ ዙሪያ በሞምባሳ እየመከሩ መሆኑን ጋዜጣው አመልክቷል።
የኬንያ የሃገር ውስጥ ሚኒስትር የሆኑት ኪኬሴሪ ሁለቱ ሃገራት በተለያዩ ጊዜያት የድንበር ግጭቶችን ዕልባት ለመስጠት ስምምነቶችን ሲፈራረሙ፣ ስምምነቶቹን ተግባራዊ በማድረጉ ረገድ ውጤት ሊመጣ አለመቻሉን አስረድተዋል።
ሁለቱ ሃገራት እንደፈረንጆቹ አቆጣጠር በ1970 የደረሱት የድንበር ስምምነትን ዳግም ለማጤን አስፈልጎ እንደነበር ገልጸዋል።
ይሁንና ሚኒስትሩ ስምምነቱን አስመልክቶ ዝርዝር መረጃን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የጋራ ጥቅሞቻችንን ለማስጠበቅ ይረዳ ዘንድ የተደረሱ ስምምነቶችን በተደጋጋሚ ማጤን ይኖርብናል ሲሉ የኬንያው የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አክለው ተናግረዋል።
ሁለቱ ሃገራት 811 ኪሎሜትር የሚገመት የድንበር ግዛት የሚያዋስናቸው ሲሆን፣ በእስካሁኑ ሂደት 43 ኪሎሜትር የሚሸፍነው ይዞታ ብቻ መቃኘት እንደቻሉ ተገልጿል።
የተቀሩ አዋሳኝ ድንበሮች ለመመርመር ከ40 አመት በላይ እንደሚፈጅ የኬንያ ባለስልጣናት ለዴይሊ ኔሽን ጋዜጣ አስረድተዋል።