ኢሳት (ህዳር 6 ፥ 2009)
የፌዴራሉ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት የስም ማጥፋት ክስ ቀርቦበት በነበረው የኢትዮ-ምህዳር ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ላይ የአንድ አመት የእስር ቅጣት አስተላለፈ።
ከሳሽ አቃቤ ህግ ጋዜጠኛው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አመራሮች ላይ የተሳሳተ መረጃን በማሰራጨትና የስም ማጥፋት ድርጊትን ፈጽሟል ሲል ባለፈው አመት የጥፋተኝነት ብይን መስጠቱ ይታወሳል።
ከዚሁ ክስ ጋር በተገናኘ ባለፈው ሳምንት ለእስር ተዳርጎ የነበረው ጋዜጠኛ ጌታቸው በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል በሚል ፍርድ ቤቱ የአንድ አመት የእስር ቅጣት ማክሰኞ መስጠቱ ታውቋል።
የክስ ሂደቱ ባለፈው ሳምንት በታየበት ወቅት ከሳሽ አቃቤ ህግ፣ ተከሳሹ እስከ ሶስት አመት የሚደርስ የእስር ቅጣት ይተላለፍበት ሲል ጥያቄ አቅርቦ እንደነበር አዲስ ስታንዳርድ መጽሄት ዘግቧል።
የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ስር ያዋሉት ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ከወራት በፊት የእሳት ቃጠሎ አደጋ ደርሶበት በነበረው የቂሊንጦ እስር ቤት እንደሚገኝ ለመረዳት ተችሏል።
ሳምንታዊው ኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ባለፈው አመት ግንቦት ወር ለንባብ ባበቃው እትሙ የፓትሪያርኩ ጽ/ቤት በሚገኝበት የቅድስት ማሪያም ገዳም በከፍተኛ አመራሮች ዘንድ ይፈጸማል ያለው ሙስናን በተመለከተ ሰፊ ዘገባን አቅርቦ እንደነበር መጽሄቱ በዘገባው አውስቷል።
አለም አቀፍ የጋዜጠኛ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የኢትዮጵያ መንግስት በተለያዩ ጊዜያት ለእስር የሚዳርጋቸው ጋዜጠኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ይገልጻሉ።
በአሁኑ ወቅትም ከ10 የሚበልጡ ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገው የሚገኙ ሲሆን፣ አገሪቱ በአለማችን ለጋዜጠኞች ምቹ ካልሆኑ 10 አገራት መካከል ግንባር ቀደም መሆኗ ይነገራል።