የኢሳት 7ኛ አመት በቦስተንና ሂውስተን ተከበረ

(ኢሳት ዜና–ሕዳር 26/2010) 

የኢሳት 7ኛ አመት በቦስተንና ሂውስተን ከተማ በድምቀት ተከበረ።

የበአሉ ተሳታፊዎች ኢሳት የሚያደርገው ትግል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያለማቋረጥ ድጋፋችንን እናደርጋለን ሲሉ ቃል ገብተዋል።

ባለፈው ቅዳሜ ታህሳስ 2/2017 በሰሜን አሜሪካ ማሳቹሴትስ ግዛት ቦስተን ከተማና ቴክሳስ ግዛት ሂውስተን ከተማ የኢሳት 7ኛ አመት በርካታ የኢሳት ደጋፊዎች በተገኙበት ተከብሯል።

ለኢሳት ማጠናከሪያ የሚሆን የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በእለቱ ተካሂዷል።

በቴክሳስ ሂውስተን በተካሄደው ዝግጅት ላይ ላለፉት አራት አመታት የሂውስተን ኢሳት ድጋፍ አስተባባሪ ኮሚቴ አባላት በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አራት የኮሚቴ አባላት እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

መድረኩን ታዋቂው ድምጻዊ መሃሪ ደገፋው በተለያዩ ጣዕመ ዜማዎቹ ድምቀትን በመስጠት ታዳሚዎችን አዝናንቷል።

በዝግጅቱ ላይ የተገኘው የኢሳት ባልደረባ ጋዜጠኛ ምናላቸው ስማቸው የኢሳት ጉዞና ፈተናዎቹ በሚል ርዕስ ላይ ገለጻ ሰጥቷል።

በዚህ ገለጻው ኢሳት ሁነቶችን እየተከታተለ ከመዘገብ ባሻገር አጀንዳዎችን እየቀረጸ ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያደርገው የነጻነትና ዲሞክራሲ ትግልን በመደገፍ ላይ ይገኛል ብሏል።

በቦስተን ከተማ በተካሄደው የኢሳት ሰባተኛ አመት ዝግጅት ደግሞ ኮመዲያን ክበበው ገዳና ድምጻዊ ሻምበል በላይነህ በመገኘት ለዝግጅቱ ከፍተኛ ድምቀት ሰጥተውታል።

የኢሳቱ ባልደረባ አቶ ኤርሚያስ ለገሰ ፥የኢትዮጵያ ህዝብ ትግልና የኢሳት ሚና” በሚል ርዕስ ንግግር አድርጓል።

በንግግሩም የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያደርገው ትግል በንዴትና ቁጭት እየተሞላ በመሄዱ ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እየተሸጋገረ መሆኑን አውስቷል።

ኢሳት አንዱ “የትግል ማዕከል” እንደመሆኑ መጠን ቅኝቱም በዛ ልክ መሆን እንዳለበት አሳስቧል።

ይህንንም ተልዕኮ ለመፈጸም የፋይናንስና ሪሶርስ ድጋፍ ያስፈልገዋል ብሏል።

በሂውስተን ከተማ በተካሄደው ዝግጅት ላይ ከጨረታና ሌሎች የገቢ ማስገኛ ዝግጅቶች ከ25ሺ ዶላር በላይ የተገኘ ሲሆን በቦስተን ከተማ ደግሞ ከ20ሺ ዶላር በላይ ተሰብስቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለም በሕዳር 25/2017 በኦሃዩ በተከበረው የኢሳት 7ኛ አመት ዝግጅት ላይ በጠቅላላው ከ20ሺ የአሜሪካን ዶላር በላይ መገኘቱን የዝግጅቱ አስተባባሪዎች ለኢሳት ገልጸዋል።

በቀጣይም የኢሳት ሰባተኛ አመት ክብረ በአል ቅዳሜ ታህሳስ 9/2017 በቴክሳስ ዋና መዲና ሆስተን እንደሚካሄድ አስተባባሪ ኮሚቴው አስታውቋል።