(ኢሳት ዜና –መስከረም 3/2010) የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥንና ሬዲዮ/ኢሳት/7ኛ አመት በሴንትሊዊስ ሚዙሪ በድምቀት ተከበረ።
በአሉ ሲከበርም ኢሳት በ7 አመት ጉዞው የተጎናጸፋቸው በርካታ ድሎች ተነስተዋል ያጋጠሙት ችግሮችም ተዳሰዋል።
ኢሳት የተመሰረተበትን 7ኛ አመት በማስመልከት በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶችና አህጉራት እየተካሄደ ያለው ዝግጅት ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን ቅዳሜ መስከረም 9/2017 በሚዙሪ ግዛት ሴንትሊዊስ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።
ከኢትዮጵያ አዲስ አመት ጋር ተያይዞ በተዘጋጀው በዚህ አመታዊ ፕሮግራም ላይ ጥሪ የተደረገላቸው የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል።
በክብር እንግድነትም የኢሳት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል ተወካይ ዶክተር ሰለሞን ረታ፣የኢሳት ባልደረባ አቶ ኤርሚያስ ለገሰና የፍልስፍና መምህሩ ዶክተር ተድላ ወልደ ዮሃንስ ተገኝተዋል።
የኢሳት የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍል ተወካይ ዶክተር ሰለሞን ረታ ባለፉት ሰባት አመታት ኢሳት ያደረገው ጉዞ በርካታ ድሎችን የተጎናጸፈበትና በርካታ ፈተናዎችን የተጋፈጠበት እንደነበር አስታውሰዋል።
ለሁሉም ኢትዮጵያውያን አይንና ጆሮ በመሆን እያገለገለ ያለው ኢሳት በ7 አመት ውስጥ ከ27 ጊዜ በላይ ከተለያዩ ሳተላይቶች ላይ የመውጣትና መውረድ ችግር አጋጥሞት እንደነበር አስታውሰዋል።
በአመት ውስጥ በአማካይ አራት ሳተላይት መቀየር ከፍተኛ የፋይናንስ ጫና እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
አገዛዙ በሚሊዮኖች የሚጠጋ ገንዘብ እየከፈለ ኢሳትን ለማፈን ጥረት ቢያደርግም በኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍና እርዳታ ኢሳት የቀጠለበት ሁኔታ እንዳለ ተናግረዋል።
አሁንም ኢሳት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከቋሚ አባልነት ጀምሮ በሚዘረጉ የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ዘዴዎች ኢሳትን እንዲረዱ ጥሪ አቅርበዋል።
የፍልስፍና መምህሩ ዶክተር ተድላ ወልደዮሐንስ ኢትዮጵያዊነት ጥያቄ ውስጥ በገባበትና ልዩነት በሚሰበክበት ሰአት ኢሳት መኖሩ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን በመልእክታቸው ገለጸዋል።
የኢትዮጵያዊነት ባህል ማለት የሁሉም ብሔረሰቦች ቋንቋ፣ባህልና እሴቶች ድምር ውጤት የሚገለጽበት እንደሆነም አመልክተዋል።
የኢሳት ባልደረባው አቶ ኤርሚያስ ለገሰ አሁን ያለንበት ወቅት ለአገዛዙ የከፍታ ወይንስ የመጨረሻው ዘመን በሚል ርእስ ገለጻ አድርገዋል።
የህወሃት አገዛዝ አሁን ያለበት ደረጃን ለማሳየት ያለፈውን አመት ችግሮች ማየት ብቻ በቂ እንደሆነ የገለጹት አቶ ኤርሚያስ በኢትዮጵያ ያለውን ረሃብ፣ስደት፣ከአካባቢ መፈናቀል ፣የገንዘብ ሽሽት፣ዝርፊያና ሌብነትን በምሳሌነት አንስተዋል።
በዘር ላይ የተመረኮዘው ኢፍትሃዊነት፣የጎሳና ድንበር ግጭት ኢትዮጵያን አደጋ ላይ እየጣላት እንደሄደ አብራርተዋል።
ይሄም የከፍታ ሳይሆን የሚያስፈራ ዘመን እየመጣ እንደሆነ አመላክተዋል።
በዝግጅቱ ላይ ኮሜዲያን ክበበው ገዳ፣ድምጻዊ እያዩ በሌ፣ድምጻዊ ንጉሱ ታምራት እንዲሁም ሙዚቀኛ ዳንኤል ወልደገብርኤል በአሉን አድምቀውት ውለዋል።