ኢሳት (ግንቦት 29 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥኝና ሬዲዮ (ኢሳት) 6ኛ ዓመት በዋሽንግተን ዲሲና በዳላስ ቴክሳስ በድምቀት ተከበረ። በተለይ በዋሽንግተን ዲሲ በተከበረው የኢሳት 6ኛ አመት ዝግጅት የኢሳት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ለነበሩት አቶ ነዓምን ዘለቀና አክቲቪስት ታማኝ በየነ ለኢሳት ላበረከቱት ልዩ አስተዋጽዖ የምስጋና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
በዋሽንግተን ዲሲና አጎራባች ግዛቶች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በታደሙበትና ግንቦት 28, 2008 በተከበረው የኢሳት 6ኛ አመት ክብረ በዓል የኢሳት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ጋዜጠኛ አበበ ገላው፣ ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙና፣ ጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና የኢሳትን ጉዞ ከኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድ ንግግር አድርገዋል። ታዋቂው ኮሜዲያን ክበበው ገዳ ለዝግጅቱ ከፍተኛ ድምቀት የሰጠ ሲሆን፣ ድምጻዊ ደሳለኝ መልኩ የሙዚቃ ስራዎቹን በማቅረብ ለኢሳት አንድነቱን አሳይቷል።
በተመሳሳይ ቅዳሜ ግንቦት 27 ፥ 2008 በቴክሳስ ግዛት ዳለስ ከተማ በተካሄደው የኢሳት 6ኝ አመት ክብረ በዓል ጋዜጠኛና መምህርት ርዕዮት አለሙ በእንግድነት የተገኘች ሲሆን፣ ኮሜዲያን ክበበው ገዳም ኪነ-ጥበባዊ ስራዎቹን በማቅረብ የኢሳት 6ኛ ዓመት በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር አድርጓል።