(ኢሳት ዲሲ–ጥር 8/2011) የኢራኑ ፕረስ ቲቪ ጋዜጠኛ በቁጥጥር ስር መዋሏን የቴሌቭዥን ጣቢያው አስታወቀ።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ርምጃውን አውግዟል።
ዕሁድ ዕለት በሴንት ሉዊስ ከተማ ሴንት ሉዊስ አውሮፕላን ማረፊያ ላይ በቁጥጥር ስር የዋለችው የ59 ዓመቷ አሜሪካዊት ማርዚ ሐሺሚ በምን ምክንያት እንደታሰረች አልታወቀም።
በትውልድ አሜሪካዊት የሆነችውና ዕምነቷን ወደ እስልምና ከመቀየሯ በፊት ሜላት ፍራንክሊን በመባል የምትታወቀው ማርዚ ሐሺሚ ለአራት መንግስታዊ ቴሌቭዥን ጣቢያዎች በእንግሊዘኛ ቋንቋ ፕሮግራም ውስጥ በመሳተፍ ላይ ትገኛለች።
ቤተሰቿን ለመጎብኘት ከቴህራን ወደ ሴይንት ሉዊስ ያቀናችው ማርዚ ሐሽሚ ሴንት ሉዊስ አውሮፕላን ማረፊያ ከተያዘች በኋላ ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ወህኒ መዛወሯ ተመልክቷል።
የምትሰራበት የኢራኑ ፕሬስ ቴቪን ጠቅሶ አልጀዚራ እንደዘገበው የ59 ዓመቷ ማርዚ ሐሽሚ ከተያዘችበት ግዜ ጀምሮ ከቤተሰቦቿ ጋር እንድትገናኝ አልተፈቀደም ሆኖም ከሁለት ቀናት በኋላ ልጇን እንድታገኝ ተደርጓል።
ጋዜጠኛዋ በካቴና እና በሰንሰለት መታጠሯን ለልጇ የገለጸች ሲሆን እያስተናገዱኝ ያሉት እንደወንጀለኛ ነው ማለቷም ተመልክቷል።
ከእሁድ ጀምሮ በእስር ቤት ስትቆይ በእስልምና የማይፈቀደው የአሳማ ስጋ እንደቀረበላትና በዚህም ሳቢያ ደረቅ ምግቦችን ብቻ ለመብላት መገደዷን ከዘገባው መረዳት ተችሏል።
የኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የጋዜጠኛዋን እስርና አያያዟን በማውገዝ መግለጫ ሰጥቷል።