የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባውን ሊያደርግ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ግንቦት 27/2010) የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ የፓርቲው ሊቀመንበር ከሆኑ ወዲህ የመጀመሪያውን ስብሰባ ሊያደርግ መሆኑ ተገለጸ።

ውስጣዊው ክፍፍል እየተባባሰ መሄዱ እየተነገረ ባለበት በአሁኑ ወቅት የተጠራው የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ለሁለት ቀናት የሚቆይ መሆኑም ተመልክቷል።

ነገ ማክሰኞ የሚጀምረውና ለሁለት ቀናት የሚካሄደው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሜቴ ስብሰባ በመንግስት መገናኛ ብዙሃን እንደተገለጸው የ2አመት ተኩል የትራንስፎርሜሽን እቅድን ለመገምገም ነው።

ሆኖም በፓርቲና በመንግስት መገናኛ ብዙሃን ከተገለጸው በተለየ በገዢው ፓርቲ ውስጥ ያለው ልዩነት እየሰፋ መምጣቱ ለስብሰባው መጠራት ምክንያት መሆኑን ቅርበት ያላቸው ወገኖች ይገልጻሉ።

የእስረኞች መፈታት፣የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የማንሳት ሒደትና ሌሎች ጉዳዮች በሕወሃት መሪዎችና በሌሎቹ መካከል የልዩነት ነጥብ ሆነው መቀጠላቸው ተመልክቷል።

የኢሕአዴግ ሊቀመንበርነትን ከሁለት ወራት በፊት በመያዝ በጠቅላይ ሚኒስትርነት 60 ቀናት ያሳለፉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ መንገድ እያፈነገጡ ኒዮ ሊብራል አስተሳሰብ እያራመዱ ነው በሚል በሕወሃት ሰዎች እየተተቹ መሆናቸውም ይታወቃል።

አሁን በኢሕአዴግ ውስጥ አለ በሚባለው የሃይል አሰላለፍ ኦሕዴድና ብአዴን የተወሰኑ የደኢሕዴን አባላትን ይዘው በአንድ ወገን በለውጥ መስመር ላይ መቆማቸው ተገልጿል።

ሕወሃት ከደኢሕዴን አቶ ሽፈራው ሽጉጤንና ሌሎች የተወሰኑ የደኢሕዴን አባላትን በመያዝ የሕወሃትን የበላይነት በነበረበት ለማስቀጠል በመንቀሳቀስ ላይ መሆናቸው ተመልክቷል።

የኢሕአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በታህሳስ 2010 ለ17 ቀናት ካካሄደው ግምገማ በኋላ በመጋቢት ወር መጀመሪያ ላይ ተመሳሳይ ስብሰባ በማድረግ አቶ ሃይለማርያምን የሚተካ ሰው ወደ ማስመረጥ መሄዱ ይታወሳል።