(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 17/2010) ትናንት እሁድ የፓርቲውን ሊቀመንበር በመምረጥ ይጠናቀቃል የተባለው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ ትናንት ከተቋረጠ በኋላ እንደገና ዛሬ መቀጠሉን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ።
ስብሰባው የተቋረጠው ሕወሃት የብቻውን ስብሰባ ለማድረግ በመጠየቁ እንደሆነም ታውቋል።
በጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ምርጫ ላይ ስምምነት በመጥፋቱ አቶ ሃይለማርያም እንዲቀጥሉ በአንዳንድ ወገኖች ሃሳብ መቅረቡም ተመልክቷል።
በሳምንቱ አጋማሽ ይጠናቀቃል የተባለው ስብሰባ ወደ ሳምንቱ መጨረሻ ቢገፋም በተባለውና በተነገረው መሰረት የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ምርጫን ማድረግ አልተቻለም።
አቶ ሃይለማርያምን ተክቶ የድርጅቱ ሊቀመንበር ብሎም የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆነውን ሰው ለመሰየም በተለይ በሕወሃትና በኦሕዴድ መካከል ያለው የሰፋ ልዩነት ለስብሰባው መራዘም በኋላም መቋረጥ ምክንያት መሆኑ ተመልክቷል።
የሕዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ መሪዎችና ቡድኑ አቶ ደመቀ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ብርቱ ግፊት ቢያደርጉም የተወሰኑ የብአዴንና የደኢሕዴን አባላትን ጨምሮ በርካታ የኦሕዴድ አባላት ሃሳቡን ተቃውመዋል።
አንዳንድ የኦሕዴድ አባላት እንዲሁም የብአዴንና የደኢሕዴን አመራሮችም ከሕወሃት ጎን የተሰለፉ ቢሆንም ከሌላ ወገን የሚመጣውን ተቃውሞ በቀላሉ መመከት እንዳልቻሉም ተመልክቷል።
የሕወሃት ሰዎች ዶክተር አብይ አሕመድን ለመቀበል አለመፍቀዳቸው ለሒደቱ መስተጓጎልና አጣብቂኝ ውስጥ መግባት በምክንያትነት ተጠቅሷል።
ሃገሪቱ የገባችበትን ቀውስ ለሕወሃት ሙሉ በሙሉ በሚታዘዘው ደመቀ መኮንን ወይንም መሰል ሰው ልንሻገረው አንችልም የሚሉት ወገኖች ደግሞ ከዶክተር አብይ ውጪ አማራጭ እንደሌለ አጽንኦት መስጠታቸው ነገሩ እንዳይቋጭና ለግዜው እንዲቋረጥ ምክንያት እንደሆነም መረዳት ተችሏል።
ትናንት ዕሑድ ተቋርጦ ዛሬ የቀጠለው ስብሰባ ነገ እንደሚጠናቀቅም የሕወሃት ደጋፊዎችም ጽፈዋል፡የትናንቱ ስብሰባ የተቋረጠው የህወሃት አባላት ለብቻቸው ለመሰብሰብ በመጠየቃቸው እንደሆነም ታውቋል።
ከአቶ ደመቀ ወይንም ከአቶ ሽፈራው ሽጉጤ ውጭ የዶ/ር አብይን መመረጥ ሲቃወም የነበረው የሕወሃት ቡድን በተናጠል ስብሰባው የአቋም ለውጥ ሰለማድረጝ አለማድረጉ የታወቀ ነገር የለም።የህወሃት አባላት እና ደጋፊዎች አይጋ ፎረም እና ትግራይ ኦንላይን በተባሉ ድረ ገጾች እንዲሁም በአንዳንድ ማህበራዊ መድረኮች በዶ/ር አብይ ላይ ውግዘታቸውን ቀጥለዋል።
አንዳንድ ወገኖች ደግሞ አቶ ሃይለማርያም መልቀቂያቸውን እንዲስቡ እና በስፍራው እንዲቀጥሉ ሃሳብ ማቅረባቸው ተመልክቷል።የተለየ ሁኔታ ካልተፈጠረ የምርጫው ውጤት ነገ ይታወቃል።