ግንቦት 20ን ለማክበር 2 ቢሊዮን ብር ተመደበ

ኢሳት (ግንቦት 16 ፥ 2008)

በሳምንቱ መጨረሻ የሚከበረውን የኢህአዴግ 25ኛ ዓመት በዓል ለማክበር 2 ቢሊዮን ብር መመደቡ ታወቀ።

ለበዓሉ አከባበር በቀበሌ መዋቅር ለወጣቶችና ለሴቶች ማህበራት ከፍተኛ ገንዘብ ተመድቧል። በሃገር ቤት ለሚታተሙ ጋዜጦች እንዲሁም  ለኤፍ ኤሞችም ገንዘብ የተደለደለ ሲሆን፣ እነዚህ መገናኛ ብዙሃን ግንቦት 20ን በተመለከተ ፕሮግራሞችን እንዲሰሩ እንዲሁም የማስታወቂያ አገልግሎት እንዲሰጡ ክፍያ እንደተፈጸመላቸው ምንጮች ለኢሳት ገልጸዋል።

የኢህአዴግ 25ኛ ዓመት በማስመልከት በትዕይንቱ ለሚታደሙ ከናቴራዎችና መፈክሮች እንዲሁም ልዩ ልዩ ቁሳቁሶችን ለማተም ንብረትነቱ የአቶ በረከት ስምዖን ባለቤት ወ/ሮ አሰፋ ፈንቴ ለሆነው ማተሚያ ቤት መስጠቱም ተመልክቷል።

በህዳር ወር 2008 በጋምቤላ ለተከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን ለሰጡት የህትመት አገልግሎት 50 ሚሊዮን ብር እንደተሰጣቸው የተገለጸው ወ/ሮ አሰፋ ፈንቴ ለዚህ ዝግጅት ምን ያህል እንደተከፈላቸው ለጊዜው የታወቀ ነገር የለም።

ከመገናኛ ብዙሃን የግንቦት 20ን በዓል በማስመልከት ዘገባና ፕሮግራም እንዲሰሩ ክፍያ የተፈጸመላቸው ጋዜጠኞች ሪፖርተር፣ ሰንደቅ እና ኢትዮቻናል ጋዜጦች ሲሆኑ፣ ሁሉም ኤፍ ኤም ሬዲዮኖች ለሚሰሩት የፕሮፓጋንዳ አገልግሎት ክፍያ እንደተፈጸመላቸው ተመልክቷል።

ለኢህአዴግ 25ና ዓመት በግል ከንግዱ ማህበረሰብ ገንዘቡን በማዋጣት ወጪውን ከሸፈኑት በዋናነት ይጠቀማሉ በሚል የኢሳት ምንጮች ስማቸውን የዘረዘሯቸውን ሃብታም ነጋዴዎች ውስጥ በላይነህ ክንዴ፣ ብዙአየሁ ታደለ፣ ትልቅሰው ገዳሙ እንዲሁም ተክለብርሃን አምባዬ እና ሰሚር አርጋው ናቸው። ሌሎችም በየደረጃው ገንዘብ ማዋጣታቸውንም ለመረዳት ተችሏል።