የኢህአዴግ ካድሬዎች ወጣቶች ብድር እንዲወስዱ እየለመኑ ቢሆንም ወጣቶቹ ግን “ መሸንገያ ነው” በማለት አልተቀበሉትም
(ኢሳት ዜና ማጋቢት 12 ቀን 2010 ዓ/ም) በአገሪቱ የሚካሄደውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ የወጣቱን ቁጣ ያበርዳል በሚል ወጣቶች ብድር እንዲወስዱ እየተጠየቁ ነው። ከአዲስ አበባ ውጭ በሚገኙ ከተሞች፣ የኢህአዴግ ካድሬዎች ቤት ለቤት እየሄዱ ወጣቶችን ብድር ውሰዱ እያሉ በመለመን ላይ ናቸው። ወጣቶች እንደሚሉት ባልተዘጋጁበትና በገንዘቡ ምን እንደሚሰሩ በውል በማያውቁበት ሁኔታ ገንዘብ ውሰዱ መባላቸው ወጣቶች ያነሱትን የለውጥ ጥያቄ ለመቀልበስ ነው በማለት ውድቅ እያደረጉት ነው።
ከዚህ ቀደም ለወጣቶች ፈንድ በሚል የተመደበው ገንዘብ በባለስልጣናት እና በዘመዶቻቸው መመዝበሩን የሚናገሩት ወጣቶች፣ በድጋሜ የስራ እድል ፈጠራ በሚል ወጣቱን ለመሸንገል የሚደረገው ሙከራም አይሳካም ይላሉ።
ወጣቱ የሰብአዊ መብቱ እየተረገጠ “ ብድር ውሰድ” መባሉ ሽንገላ ነው የሚሉት ወጣቶች፣ አገዛዙ “ የስራ ፈጠራ” እያለ ከሚናገር ዝም ቢል ወይም ሰብአዊ መብቱን ቢያከብርለት እንደሚመርጡ ይናገራሉ። የኢህአዴግ አባል የሆኑ ወጣቶች ሌሎችን ወጣቶች ለማሳመን እንደሚከብዳቸውም ይገልጻሉ።
የወጣት ተወካዮች “ ባለስልጣናት ለራሳቸው ጥቅም ከማመቻቸት ውጭ ለወጣቱ አስበው” አይሰሩም የሚሉት ወጣቶች፣ እነሱ ገንዘብ መስጠት ለሚፈልጉት ሰው መንገዱን አልጋ በአልጋ ያደርጉታል፣ መስጠት ለማይፈልጉት ሰው ደግሞ መንገዱ ተራራ ነው ይላሉ።
ለወጣቱ እየተባለ የሚመደው ገንዘብ በአየር ላይ እንደሚቀር የድርጅቱ ተራ አባላት ብቻ ሳይሆን በመካከለኛ ደረጃ ተቀመጡ አመራሮችም እየገለጹት ነው። “ ተሃድሶ ይባላል እንጅ ታምሶ ነው” የሚሉት እነዚህ አመራሮች፣ በተሃድሶ ወቅት ለወጣቱ ስራ ፈጥረናል እየተባለ የሚወራው ሃሰት ነው፤ ወጣቱ ስራ ቢፈጠርለት ኖሮ በድንጋይ ባልተወራወረ ነበር” ሲል ያክላሉ።