የኢህአዴግ አመራሮች ቀደም ብለው የነበሩትን መንግስታት በማንኳሰስ የራሳቸውን ስራ ማሞገስ በየመድረኩ ተጠናክሮ መቀጠሉ አግባብ እንዳልሆነ ተነገረ፡፡

ጥቅምት ፲፩(አስራ አንድ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ በቅርቡ በአዳማ ከተማ   ለጋዜጠኞች ባዘጋጀው ሴሚናር ከኢትዮጵያ ስፖርት ኮሚሽን ተወክለው በስብሰባው በመገኘት ንግግር ያደረጉት አቶ ናስር ለገሰ ባቀረቡት የኢትዮጵያ ሰፖርት ታሪክ ንግግራቸው የቀደሙት መንግስታትን ስራ በማጣጣል የገዢውን መንግስት ስራ በማግዘፍ ባቀረቡት ጽሁፍ ከጋዜጠኞች ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶባቸዋል፡፡

የገዢው መንግስት አሁን የሚያንቀሳቅሰው ከፍተኛ በጀት ስፖርቱ እንዲጎለብት ለማድረግ ከልብ ከመጣር ይልቅ ስፖርቱን ለፖለቲካ ዓላማው ማራመጃ በማድረግ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ከመንግስት ሰራተኛው  ደሞዝ በፐርሰንት በመቁረጥ እና ህዝቡን በማስገደድ በመሰብሰብ የሚገኘውን ሃብት ለብክነት እየዳረገው መሆኑን ጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት ከህዝብ ገንዘብ ሳይሰበሰብ በበጎ ፈቃደኞች በመታገዝ በኦሎምፒክ መድረክ ይዘናቸው የቀረብናቸው የቦክስ ፣ብስክሌትና የመሳሰሉት ስፖርቶች ዛሬ የሉም ሲሉም ተደምጠዋል፡፡

ʻበአሁኑ ሰዓት ገዢው መንግስት እየተጠቀመባቸው ያሉት አብዛኛው የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች በቀደሙት መንግስታት የተሰሩ መሆኑስ እንዴት ይረሳል?ʼ በማለት ጋዜጠኞች ጠይቀዋል፡፡

ገዢው መንግስት ለደጋፊዎቹ እና ለጥቂት የስርአቱ ደጋፊዎች ለስፖርት ማዘውተሪያ ግንባታ የሚውል ቦታ ቢሰጥም አብዛኞች ታጥረው አመታትን ሲያስቆጥሩ አንዳንዶች የሰሩት ጂምናዚየም ሰፊው የስፖርት ማህበረሰብ ገብቶ ሊሰራባቸው የማይችል ለጥቂት ባለ ገንዘቦች ብቻ የተዘጋጁ በመሆኑ የስፖርት ልማት ግንባታዎች ተብለው እንደማይቆጠሩ ገልጸዋል፡፡

የግል ሚዲያውን በማዋከብ ያለባችሁ ጉድለት እንዳይነገር ትከለክላላችሁ ያሉት የልሳን ጋዜጣ አዘጋጅ  ʻበራሳችን ተነሳሽነት ዘገባውን ተከታትለን ለመስራት በየቦታው ተዘዋውረን ስንመለከት  በሪፖርት የምትገልጹትን በተግባር ተሰርቶ አናገኝም፣ ይህን ጉድለት በጋዜጣና መጽሄቶች ለህዝብ ይፋ በማድረግ ዘገባዎች ስናቀርብ ስማችን ጠፋ በማለት ወደ ክስ ትሮጣላችሁʼ  በማለት አስተየየት ስጥቷል።

“ በታዳጊዎች የእጅ ፣የመረብ ኳስና የመሳሰሉት ስፖርቶች ላይ የታዘብነውም ዕድሜያቸው ከወጣትነት ያለፉ ሰልጣኞች የሚሰለጥኑበት  ሁኔታ በግልጽ እየታየ የሚፈለገውን ተተኪ የማግኘት ሂደቱ እንዴት ይሳካል? ”በማለት በማሰልጠኛ ጣቢያዎች የታዘቡትን ተናግረዋል፡፡

“ በተለያዩ ክልሎች ባሉ የስፖርት ማዕከላት ሃያ ሽህ ታዳጊ ወጣቶች እየሰለጠኑ ነው ” በሚለው የሃላፊው ንግግር ዙሪያም “አሉ እየተባለ የሚዎራላቸው ማእከሎች ላይ ምንም አይነት የስፖርት ግብአት እና ትጥቅ ያልተሟላባቸው መሆኑን በአካል አይተናል፡፡ ሰልጣኞች ጂንስ ሱሪ ቆርጠው ቁምጣ በማድረግ ሲሰሩ እያን እንዴት በተሟላ ሁኔታ ስልጠና እየሰጠን ነው ብላችሁ ትናገራላችሁ? ” በማለት ፈታኝና በማስረጃ የተደገፉ ጥያቄዎች አቅርበው ምልሽ ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡

ባለ ሃብቱን በማበረታታት ዙሪያ መንግስታቸው እየሰራ መሆኑን አቶ ናስር ቢናገሩም ከጋዜጠኞች የተሰጣቸው ምላሽ ግን በተቃራኒው ነበር፡፡ በሃገረ ሰላም ከተማ የጀግናው አበበ ቢቂላ ቤተሰቦች በስፖርቱ መስክ ለመሰማራትና መዋእለ ነዋይ ለማፍሰስ ለረዢም ጊዜ ያቀረቡት ጥያቄ ለበርካታ አመታት ምላሽ የተነፈገው መሆኑን የተናገሩት ጋዜጠኖች በርካታ አገልግሎት የሚሰጡት ለአመራር ቤተሰቦችና ለስርአቱ አቀንቃኞች ብቻ መሆኑን በተለያዩ ቦታዎች በተከሰቱ ድርጊቶች አይተናል በማለት ባለሃብቱን ለማበረታታት የሚለው መስመር የተዘጋጀው ሆን ተብሎ በየደረጃው ያለው አመራር በሙስና ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሆነ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

በስብሰባው ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ልምዳቸውን ያካፈሉት አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ በንጉሱ ዘመን የኢትዮጵያ ስፖርት የተስፋፋበት ዋና ምክንያት በትምህርት ቤቶች አካባቢ ትኩረት ተሰጥቶ ስለተሰራ እንደነበር ገልጸው ፤ የተማሪዎችን ትጥቅ  የትምህርት ሚኒስትር ይሸፍን እንደነበር አስረድተዋል፡፡በወቅቱ የነበረው ስፖርታዊ ውድድር ከዛሬው የተሸለ እንደነበር የገለጹት አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ በየሳምንቱ የፈረስ ጉግስ ፣የሞተር ሳይክል፣የብስክሌት፣የቅርጫት ፣የመረብ ኳስና የመሳሰሉት ውድድረሮች በስፋት ይካሄዱ እንደነበር በዝርዝር  ለተሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡

“ አሁን የምናየው የፌደሬሽንና ሰፖርት ኮሚሽን አመራሮች ወደ ስልጣን የሚዎጡት የፖለቲካ ታማኝነታቸው ታይቶ መሆኑ ለስፖርቱ መውደቅ ምክንያት ይመስለናል፣ በእርስዎ በኩል ያለው አስተያየት ምንድን ነው ? ” ተብሎ  ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ፍቅሩ ሲመልሱ “ፖለቲካ  አታናግረኝ ሆኖም ሁሉም በስፖርት አመራር ላይ መቀመጥ ያለባቸው ከክለብ ጀምረው በስፖርቱ ውስጥ ያደጉ ውጣ ውረዱን የሚያውቁ መሆን አለባቸው፡፡ ” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በሴሜናሩ አሁን ያሉ አመራሮች የስፖርትን ምንነት እንኳን የማያውቁ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ በጀት በአግባቡ እንደ ማይመድቡ ጋዜጠኞች ተነግሯል፡፡ ከትምህርታዊነቱ ይልቅ ወደ ክርክር ባዘነበለው የሶስት ቀን ሴሚናር  ህዝብ ግኑኝነትንና ጋዜጠኝነትን ለይታችሁ እዩ፣  የፌደሬሽኑን ጉድለት ባጋለጡ ጋዜጠኞች ላይ በሽጉጥ የተንገራገረበት ሁኔታ እያለ ወደ እናንተ መቅረብ እንዴት ይቻላል?  ለምን ተነካሁ ሳይሆን የተነካሁበት ችግሬ ምንድን ነው በማለት ማሰብ አለባችሁ የሚሉ አስተያየቶች ቀርበዋል።