የኢህአዴግ ታማኝ አባላት ናቸው የተባሉ መምህራን ተመርጠው የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና እንዲሰጡ ሊደረግ ነው

ሰኔ ፳፱ ( ሃያ ዘጠኝ ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከአንድ ወር በፊት ለከፍተኛ ትምህርት የሚያበቃው ብሄራዊ ፈተና መሰረቁን ተከትሎ፣  የድጋሜ ፈተና ያዘጋጀው ትምህርት ሚኒስቴር፣ ፈተናውን ለስርዓቱ ይታመናሉ በተባሉ መምህራን ለመስጠት በዝግጅት ላይ ነው።

ከመላው አገሪቱ በጥንቃቄ የተመረጡ መምህራን ሰኔ 28 ቀን 2008 ዓም አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን ፣ በዳግምዊ ሚኒሊክ መሰናዶ ት/ቤት ቅጥር ግቢ በጊዜያዊነት በተዘጋጀው ጣቢያ ውስጥ  ፈተናው ላይ ችግር ቢከሰት ኃላፊነት እንዲወስዱ የተዘጋጀውን ውል በተናጠል እንዲፈርሙ እንዲሁም ስልጠና እንዲወስዱ ተደርጓል።

ለሁሉም ትምህርት ቤቶች የመወዳደሪያ መስፈርት መውረዱን የገለጹት ምንጮች፣ ከመስፈርቶቹ መካከል ግን ዋናው መምህሩ ለኢህአዴግ ያለው ታማኝነት መሆኑን ይገልጻሉ። የድርጅት አባላትን ለማሳለፍ የተደረገው  ምልመላ በጥንቃቄ መከናወኑን የገለጹት እነዚሁ ምንጮች፣ በአንዳንድ  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የተወሰኑ የድርጅት አባላት ያልሆኑት ቢያልፉም ከ98 በመቶ በላይ የሚሆኑት የድርጅት አባላት ናቸው ሲሉ ምንጮች ያክላሉ።

በፌደራል በክልል እና በዞን አስተባባሪነት የበላይ ሆነው የተመደቡት አብዛኞቹ ታማኞቹ የህወሃት አባላት ሲሆኑ፣ ከቅድመ ዝግጅት በኋላና ፈተናው ሰኞ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅበት ቀን ድረስ ፈታኞቹ  በጊዜያዊነት በተዘጋጀ ካምፕ ውስጥ ይቆያሉ። ቀደም ሲል በፈታኝነት ተመልምለው የነበሩት መምህራን ታማኞች አይደላችሁም በሚል በድጋሜ እንዳይፈትኑ ተደርጓል።