የኢህአዴግ መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ያራዘመው ህዝባዊ ተቃውሞው ሊቀጣጠል ይችላል የሚል ስጋት ስላደረበት እንደሆነ ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 21 ፥ 2009)

መንግስት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲራዘም የወሰነው ህዝባዊ ተቃውሞ ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት ስላደረበትና ተግባራዊ የተደረገ ማሻሻያ ባለመኖሩ እንደሆነ ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ የተለያዩ አካላትን ዋቢ በማድረግ ሃሙስ ዘግቧል።

የዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑትና ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በፊትና በአዋጁ መውጣት ወቅት ለእስር ተዳርገው የነበራት አቶ ስዩም ተሾመ ህዝቡ ተቃውሞን የሚገልፅበት መንገድ ባለመኖሩ አዋጅ ከተነሳ ህዝባዊ ተቃውሞ ሊቀጥል እንደሚችል ከጋዜጣው ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስረድተዋል።

ከዩኒቨርስቲ መምህሩ በተጨማሪ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ በርካታ ነዋሪዎች ጥያቄያቸው ምላሽ ባለማግኘቱ የአዋጁ መነሳትን ተከትሎ ተቃውሞ እንደሚቀጥል በቅርቡ ለዋሽንግተን ፖስት ገልጸው እንደነበር ጋዜጣው በዘገባው አውስቷል።

ሃሙስ እንዲራዘም የተደረገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መንግስት ቃል በገባው መሰረት የተወሰደ ማሻሻያ አለመኖሩን የሚያሳይ ነው ሲሉ የዩኒቨርስቲ መምህሩ አቶ ተሾመ አክለው አስረደተዋል።

የአለም ባንክን ጨምሮ የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት አዋጁ የሃገሪቱ የውጭ ንግድ እንዲቀንስ ከፍተኛ አስተዋፅዖ ማድረጉን ሲገልፁ ቆይተዋል።

አሜሪካን እንዲሁም የተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት አዋጁን ምክንያት በማድረግ ዜጎቻቸው ወደ ኢትዮጵያ ከመጓዝ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የአውሮፓ ፓርላማ ለበርካታ ሰዎች ሞት ምክንያት የሆነው አዋጅ በገለልተኛ አካል ማጣራት እንዲካሄድበት በማሳሰብ ላይ ናቸው።